የሆስፒታሎችን ደረጃ በማሻሻል ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ ነው...ዶክተር ሊያ ታደሰ

76

ደሴ፤ ጥር 07/2013(ኢዜአ) የሆስፒታሎችን ደረጃ በማሻሻል ጥራት ያለውና የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

በኮምቦልቻ ከተማ 178 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ የተገነባው የኮምቦልቻ ጠቅላላ ሆስፒታል ዛሬ  ሲመረቅ ሚኒስትሯ እንደገለጹት መንግስት የጤና ዘርፉን ለማሻሻል በትኩረት እየሰራ ነው።

ለህብረተሰቡ ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆን ከደረጃ በታች የነበሩ ሆስፒታሎችን ደረጃ በማሻሻል ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ለዚህም የህክምና ዘርፉን ለማዘመን አዳዲስ አሰራሮች ተቀርፀው ከክልሎች  ጋር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለተገነቡ በርካታ ሆስፒታሎችም አስፈላጊው ግብዓት ተሟልተቶላቸው ለህብረተሰቡ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል ያሉት ዶክተር ሊያ፤ ህብረተሰቡም የተገነቡ የጤና ተቋማትን በመጠበቅና በመንከባከብ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ ኃላፊነቱን እንዲወጣም አመልክተዋል።

የኮሮና ቫይረስ እንደገና እየተስፋፋ ያለበት ወቅት በመሆኑም ሁሉም ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሱን ከቫይረሱ ሊከላከል ይገባል ብለዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ በበኩላቸው የክልሉ ህዝብ የተሻለ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ ከፌዴራል መንግስት ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የጤና ተቋማት እጥረት ባለባቸው የክልሉ አካባቢዎች እንዲገነቡ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው በደቡብ ወሎ ዞን ሰሞኑን የተመረቁ ሶስት ሆስፒታሎችም የዚሁ አካል እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

ሆስፒታሎቹ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻልም አስፈላጊው ግብዓት እንዲሟላላቸው እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ዶክተር ከማል መሃመድ እንዳሉት በከተማዋ ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል 178 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ የተገነባው የኮምቦልቻ ጠቅላላ ሆስፒታል ከ200 በላይ የህሙማን አልጋዎች አሉት። 

ሆስፒታሉም ለደቡብ ወሎና ኦሮሞ ብሄረሰብ ዞኖች እንዲሁም ለአፋር አጎራባች አካባቢ ህዝብ ጨምሮ አገልግሎቱን ተደራሽ ያደርጋል ብለዋል።

የህክምና ቁሳቁሶች ተሟልተውለት በቅርቡ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል ከተማ አስተዳደሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ኃላፊነቱን እንደሚወጣም አስታውቀዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን ከአንድ ቢሊዮን 600ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነቡ የተለያዩ የመሰረተ ልማትና ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ፕሮጀክቶች የፌዴራል፣ ክልልና ዞን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ዛሬና ትናንት እንደተመረቁ ቀደም ሲል ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም