ከምርጫ ጋር ተያይዞ ሊፈጸሙ የሚችሉ ወንጀሎችን መመርመር የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው ... የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ

63

አዲስ አበባ፣ ጥር 7/2013 ( ኢዜአ) ምርጫን ተከትሎ ሊፈጸሙ የሚችሉ የወንጀል ተግባራትን መመርመር የሚያስችል ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስታወቀ፡፡ 

በአዲሱ የምርጫ ሕግ ላይ ለክልል ዓቃቢያነ ሕግ፣ ለፌዴራልና ለክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች አመራሮችና ባለሙያዎች በአዲስ አበባ ስልጠና እየሰጠ ነው፡፡ 

ምርጫ ትክክለኛ ዴሞክራሲ ለመተግበር ሁነኛ መሳሪያ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ፈቃዱ ጸጋ መጪው ምርጫ በሠላም እንዲካሄድ ባለሙያዎችን ከማሰልጠን ጀምሮ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

መድረኩ ሰልጣኞች ከምርጫ ጋር በተያያዘ የሚከሰትን የወንጀል ተግባር ለመመርመር የሚያስችላቸውን እውቀትና ክህሎት የሚያገኙበት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ 

ስልጠናው በሕገ መንግስቱ የተካተቱትን አንቀፆች ጨምሮ በምርጫ ዙሪያ የወጡ አዋጆች እንዲተገበሩና ፍትሃዊ የምርጫ ሂደት እንዲኖር አጋዥ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ባላደገባት ቀርቶ በኃያላን አገራትም ሳይቀር ምርጫ ውዝግብ ሊገጥመው ይችላል ብለዋል አቶ ፈቃዱ፡፡ 

ሕግ አውጪው አካልም ምርጫ እንዴት መከናወን እንዳለበት ሕግ ከማውጣት ጎንለጎን በምርጫ ሂደት የሚከሰቱ ወንጀሎች ካሉ ማስቀጣት በሚችሉበት ሁኔታ መደንገጉንም አመልክተዋል፡፡ 

"የፍትህ አካሉም የምርጫ አዋጁን ጠንቅቆ በማወቅ ምርጫው በሠላማዊ ሁኔታ እንዲከወን የበኩሉን ሊወጣ ይገባል" ብለዋል፡፡

የስልጠናው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ለምርጫው በሠላም መካሄድ እንደሚሰሩና ሕግ ጥሶ የሚመጣ  ካለም ወደ ሕግ ለማቅረብ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ 

ከስልጠናው ስለ አዲሱ የምርጫ ሕግ 1162/2011 ሰፊ ግንዛቤ እንደሚያገኙም ነው የገለፁት።

በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አዘጋጅነት በአዲሱ የምርጫ ሕግ ላይ አተኩሮ የሚሰጠው ስልጠና ለሁለት ቀናት የሚቆይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም