የከተራና የጥምቀት በዓላት በሰላም እንዲከበሩ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ

75

አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2013(ኢዜአ) የዘንድሮ የከተራና የጥምቀት በዓላት በሰላም እንዲከበሩ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን አስታወቀ፡፡

የከተራ እና የጥምቀት በዓላት ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲከበሩ በየእርከኑ ከሚገኙ የአስተዳደር አካላት ፣ ከበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴ ፣ ከሌሎች የፀጥታ እና የፍትህ አካላት እንዲሁም የፀጥታው ዋና ባለቤት ከሆነው ሰላም ወዳዱ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ጋር እየሰራ መሆኑንኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

ህብረተሰቡ ለፀጥታ ስራው ስኬታማነት እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ኮሚሽኑ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

በዓላቱ በሰላም ተጀምረው እንዲጠናቀቁ ለወንጀል እና ትራፊክ አደጋ መከላከል ተግባር ልዩ ትኩረት በመስጠት በርካታ የሰው ኃይል ማሰማራቱን ገልፆ፤ በታቦት ማደሪያ ስፍራዎች በተለይም በርካታ የበዓሉ ታዳሚዎች በሚገኙበት ጃን ሜዳ ጊዜያዊ ፖሊስ ጣቢያ ተከፍቶ አግልጋሎት የሚሰጥ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በዓለም አቀፉ የትምህርትና የባህል ተቋም ዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስ የተመዘገበው የጥምቀት በዓል የሀገሪቱን ገፅታ ለመገንባት ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ በልዩ ልዩ መንገድ የሚተላለፉ መልዕክቶች በዓሉን የተመለከቱ ሊሆኑ እንደሚገባም ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

ከበዓሉ መንፈስና ከህገ-መንገስቱ እንዲሁም ከህግ ጋር የሚቃረኑ የሌላን ወገን መብት የሚጋፉ መልዕክቶችም ሆኑ ድርጊቶች ፍፁም ተቀባይነት እንደሌላቸው የገለጸው ኮሚሽኑ፤ ይህን ሲፈፅሙ በሚገኙ ላይ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ተብሏል።

ርችት መተኮስ ለፀረ-ሰላም ኃይሎች ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር በመሆኑ ርችት መተኮስ ፍፁም የተከለከለ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጾ፤ በዓሉ በሚከበርበት ስፍራ ምንም አይነት የጦር መሳሪያ ፣ ተቀጣጣይም ሆነ ስለት ነገሮችን ይዞ መንቀሳቀስ ክልክል መሆኑም ተጠቅሷል።

የበዓሉ ታዳሚዎችም ይህን ተገንዝበው ለፍተሻ ትብብር እንዲያደርጉ በተለይ ደግሞ በዓሉ በሰላም እንዳይከበር አንዳንድ ፀረ-ሰላም ኃይሎች የብሔር ግጭት ለማስናሳት እንደሚንቀሳቀሱ ህብረተሰቡ ተገንዝቦ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም አሳስቧል፡፡

በአንዳንድ መገናኛ ብዙኋን እና ማህበራዊ ሚዲያዎች የከተማዋን የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ የተዛባ መረጃ እየተሰራጨ ነው ያለው ኮሚሽኑ ጥር 6 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለልዩ ልዩ ፕሮግራሞች ማድመቂያ ተብሎ በመጋዘን ውስጥ ተቀምጦ የነበረ ርችት በመፈንዳቱ ከህንፃው እድሳት አጋጥሞ የነበረው እሳት ጉዳት ሳያስከትል በቀላሉ መቆጣጠር የተቻለ ቢሆንም አንዳንድ አካላት የቦንብ ፍንዳታ እንዳጋጠመ አድርገው የተዛባ ወሬ ማናፈሳቸውን ለአብነት አንስቷል፡፡

የተዛቡ መረጃዎችን በህዝብ ላይም ሆነ በአጠቃላይ በበዓሉ ድባብ ላይ አሉታዊ ተፅኖ የሚያሳድሩ በመሆኑ መረጃን ከተገቢው አካል በመውሰድ ለህዝብ ማድረስ እንደሚገባ የገለጸው ኮሚሽኑ፤ በዓሉ በሰላም እንዲከበር እየሰራሁ ነው ብሏል።

የበአሉ ታዳሚ ፀበል በሚረጭበት ወቅት በሚፈጠር ግፊያ ጉዳት እንዳይደርስበት፣ ንብረቶቹ እንዳይሰረቁበት እንዲሁም ከስፍራ ወደ ስፍራ ሲንቀሳቀስ የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበትም አሳስቧል።

የእምነቱ ተከታዮች በተለይ ወጣቶች ከዚህ በፊት እንደሚያደርጉት በተደራጀ መንገድ ከፖሊስ እና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጎን በመቆም ለበዓሉ በሰላም መከበር እያደረጉት ላለው አስተዋፅኦ ኮሚሽኑ ምስጋና አቅርቦ ትብብሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፏል፡፡

ህብረተሰቡ በማንኛው ወቅት ከፀጥታ ስራ ጋር ተያያዥ እና አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙትም ይሁን ጥቆማ ለመስጠት እንዲሁም የፖሊስ አገልግሎትን ለማግኘት በስልክ ቁጥር

01-11-26-43-77

01-11-26-43-59

01-18-27-41-51

01-11-11-01-11 እና

በ991 ነፃ የስልክ መስመር መጠቀም እንደሚቻል ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

ታቦታት በሚያልፉበት ወቅት አሽከርካሪዎች የፀጥታ አካላት ለሚሰጧቸው ተዕዛዝ የተለመደ ትብብራቸውን እንዲያደርጉ ኮሚሽኑ ጥሪ በማስተላለፍ ከጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በዓሉ እስከሚጠናቀቅ ድረስ በጃን ሜዳ ዙሪያ ተሽከርካሪ ለረጅም ሆነ ለአጭር ጊዜ አቁሞ መሄድ ፍፁም የተከለከለ መሆኑን አሽከርካሪዎች ተገንዝበው አማራጭ የማቆሚያ ስፍራዎችን እንዲጠቀሙ አሳስቧል፡፡

ለመላው የእምነቱ ተከታዮች በዓሉ የሰላም እና የጤና እንዲሆን ኮሚሽኑ መልካም ምኞቱን መግለጹን ከኮሚሽኑ ማህበራዊ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም