የክልሉ ህዝብ ሃሳቡን ወደ ልማት በማዞር የብልጽግና ጉዞን ማፋጠን አለበት ... አቶ አገኘው ተሻገር

66

ደሴ፣ ጥር 07/2013(ኢዜአ) የክልሉ ህዝብ ሙሉ ሃሳቡን ወደ ልማት በማዞር የብልጽግና ጉዞን ማፋጠን እንዳለበት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘው ተሻገር ተናገሩ።

በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳና ኮምቦልቻ ከተማ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ዛሬ ተመረቀዋል። 

ርዕሰ መስተዳደሩ በወቅቱ እንደገለጹት ፤ በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ መሰረተ ልማቶችን በመጠበቅ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥበቃ ማድረግ ይኖርበታል።

የህወሓት ጁንታ በህዝብ ትግል በመወገዱም የክልሉ ህብረተሰብ ሙሉ ሃሳቡን ወደ ልማት በማዞር የብልጽግና ጉዞን ማፋጠን እንዳለበት ተናግረዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰዒድ መሐመድ በበኩላቸው የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የተመረቁት የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ገጥመው የነበሩ አስቸጋሪ ወቅቶችን ተቋቁሞ በማጠናቀቅ ለዚህ መብቃታቸው የሚደነቅ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜና ጥራት እንዲጠናቀቁ  ህብረተሰቡ ላደረገው ያልተቆጠበ እገዛም ምስጋና አቅርበዋል።

ከዚህ በፊት የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችም በፍጥነት ተጠናቀው አግልግሎት እንዲሰጡ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ዛሬ ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል  የኮምቦልቻ ከተማ ጠቅላላ ሆስፒታል፣ ዘመናዊ ቄራ እና የቃሉ ገርባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይገኙበታል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ  የፌደራልና ክልሉ  አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

በዞኑ ትናንትም ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የተለያዩ  የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች መመረቃቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም