የህዳሴ ግድብን ከደለል ለመታደግ በሚካሄድ የተፋሰስ ልማት ስራ ህብረተሰቡ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ተጠየቀ

50

አሶሳ፣ ጥር  07 / 2013 (ኢዜአ) -የህዳሴውን ግድብ ከደለል ለመታደግ በሚካሄደው የበጋ ወቅት የተፋሰስ ልማት ስራ ህብረተሰቡ ተሳትፎውን እንዲንያጠናክር የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ጠየቁ፡፡

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የበጋ ወራት የተፋሰስ ልማት የዘመቻ ስራን በመስክ ተመልከተዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በወቅቱ እንደገለጹት የክልሉ ተፈጥሮ ሃብት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ መጥቷል፡፡

ክልሉ የህዳሴው ግድብ የሚገነባበት መሆኑን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ "በክልሉ አባይ ተፋሰስ ውስጥ ጠንካራ የተፈጥሮ ህብት ጥበቃ ሥራ ማካሄድ ይጠብቀናል" ብለዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የበጋ ወቅት የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ውጤት መገኘቱን ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል፡፡

በዘንድሮው የበጋ ወቅት የተፋሰስ ልማት 200 ሺህ ሰዎችን በማሳተፍ 32 ሺህ ሄክታር በሰው ሰራሽ ችግር የተጎዳ መሬት ለመሸፈን መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡

በክረምቱ የሚተከሉ ችግኞችም እየተዘጋጁ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በተፋሰስ ልማት ዘመቻው እየተሳተፉ ከሚገኙ የክልሉ አርሶ አደሮች መካከል ወይዘሮ መርዬም ሙሳ የአካባቢ መራቆት ለም አፈር በጎርፍ እንዲወሰድ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

"በተፋሰስ ልማት ስራ የተጎዳ መሬት አገግሞ በተግባር ውጤት አይተንበታል" ብለዋል።

"የተፋሰስ ስራን በራሳችን ተነሳሽነት እየሠራን ነው" ያሉት ደግሞ አርሶ አደር ሃሊፋ እስማኤል ናቸው፡፡

"በተፈጥሮ ሃብት ሥራው የወንዞች ውሃ መጠን እየጨመረ መጥቷል" ብለዋል፡፡

እስካሁን ያከናወኑት ተፋሰስ ልማት በጋራ መሬት ላይ እንደሆነ ገልጸው ተሞክሮውን በራሳቸው ማሳ ማካሄድ መጀመራቸውን አርሶ አደሩ ተናግረዋል፡፡

በአሶሳ ዞን የባምባሲ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዓሊ መርቀኒ በወረዳው በበጋ ተፋሰስ ስራ በተከናወነባቸው አካባቢዎች በመጪው ክረምት የሚተከሉ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ችግኞች ከወዲሁ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም