በኦሮሚያ ተፈናቃዮችን ለማቋቋም ዝግጅት ተደርጓል--- ዶክተር ነገሪ ሌንጮ

104
ባህር ዳር ሀምሌ 16/2010 ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆችን ወደ ነበሩበት በመመለስ ለማቋቋም አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ አስታወቁ። ኃላፊው በባህር ዳር ከሚገኙ ተፈናቃዮች ጋር  ከተወያዩ በኋላ  ለኢዜአ እንደገለጹት ከወራት በፊት በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረ ግጭት የአማራ ተወላጆች ከኦሮሚያ ተፈናቅለው እስካሁን ወደ ቀደሞ መኖሪያቸው አልተመለሱም። በወቅቱ ሌሎች ህዝቦችም የመፈናቀል ችግር አጋጥሟቸው እንደነበር አስታውሰዋል። የኦሮሚያ ወንድም ህዝብ የተፈናቃዮችን ንብረት፣ ሃብትና መሬታቸውን እንደራሱ በመጠበቅ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ጠቁመው፤ "አሁን አካባቢው የተረጋጋና ሰላማዊ ሁኔታ በመመቻቸቱ ተፈናቃዮች ያለምንም ስጋት ሊመለሱ ይግባል "ብለዋል። ዶክተር ነገሪ እንዳሉት በወቅቱ ችግሩ እንዲፈጠር ያደረጉት ለጥቅማቸው የቆሙ ግለሰቦችና አንዳንድ አመራሮች ናቸው፡፡ በዜጎች ላይ ጉዳት እንዲደርስ ሆን ብለው የተንቀሳቀሱ የፀጥታም ሆነ ሌሎች አመራሮችን በጥናት በመለየት  የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ በጥፋታቸውም በህግ እንዲጠየቁ እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡ "ባለፉት ወራት በተከናወነው የማጥራት ስራ በአካባቢዎቹ  የተረጋጋና አስተማማኝ ሰላም በመስፈኑ ተፈናቃዮች አብረዋቸው ከኖሩ ወንድሞቻቸው ጋር ሄደው በመቀላቀል የቀደመ ሰላማዊ ኑሯቸውን መምራት ይገባቸዋል "ብለዋል። ተፈናቃዮች ወደ አካባቢው ሲመለሱም እራሳቸውን እስኪችሉ   መጠለያ ፣ ምግብ እና  አስፈላጊው ቁሳቁሶችን በማቅረብ ለማቋቋም እንዲቻል ዝግጅት መደረጉን ዶክተር ነገሪ አስታውቀዋል። የሁለቱን ክልሎች  ህዝቦች ለዘመናት የዘለቀ ጠንካራ ግንኙነት በማሻከር ለርካሽ ፖለቲካ ጥቅም ለማዋል የሚጥሩ አካላትም ከዚሁ እኩይ ድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ አሳስበዋል። ለዘመናት ተዋደው፣ ተጋብተውና ተዋልደው በሚኖሩ ሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካካል ሊፈጠር የማይገባው ችግር መከሰቱ ተገቢ እንዳልነበር የተናገሩት ደግሞ አባ ገዳ ተሾመ በቀለ ናቸው። " በኦሮሞ ባህል መሰረት ጥፋት በጥፋት አይታረምም፤ ጥፋት በእርቅና በሰላም ነው የሚታረመው " ያሉት አባገዳ ተሾመ  የሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች እንደቀደመው ሁሉ ተዋደውና ተሳስበው በጋራ መኖር እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡ የአማራና የአሮሞ ህዝቦች በባህል፣ በቋንቋና በኃይማኖት የረጅም ጊዜ ትስስር ያላቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ችግሩ በአስተዳደር ክፍተት የተከሰተ በደል እንጂ የህዝቦች  እንዳልሆነ አመልክተዋል። የተፈጠረውን ችግር በማርገብም ዳግም እንዳይከሰት በወጣቶች፣ በሃገር ሽማግሌዎች፣በአባገዳዎች በኩል ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል። " አሁን ህዝቡ ወንድሞቹን ለመቀበል በጉጉት እየጠበቀ ነው " ያሉት አባገዳ ተሾመ ተፈናቃዮችም የተመቻቸላቸው እድል ተጠቅመው በይቅርታ መንፈስ ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው በሰላም እንደሚመለሱም መዕልክታቸውን አስተላልፈዋል። የቡኖ በደሌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ለጥይበሉ ሞቱማ በበኩላቸው ከሰባት ወራት በፊት ግለሰቦች ፈጥረውት በነበረው ችግር አብረው በሚኖሩ የአማራ፣ የትግራይና የኦሮሞ ተወላጆች ላይ ጉዳት መድረሱን  ተናግረዋል። ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ የማስተካከያ እርምጃዎችን በመውሰድ  በአሁኑ ወቅት  በአካባቢው  ከምንጊዜውም የተሻለ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ተፈጥሮ በነበረው ችግር የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆችም ወደ አካባቢያቸው ለመመለስ በቂ ዝግጅት መደረጉንና የኦሮሚያ ህዝብም ወገኖቻችን ይምጡልን በማለት የአካባቢውን አመራር ግፊት እያደረገ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል። የተፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀምም የሁለቱን ክልል ህዝቦች ለማቃቃር የሚሯሯጡ አካላት  እንዳሉና በጋራ መመከት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ ከኦሮሚያ ክልል የመጡ የአማራ ተወላጆችን መልሶ ለማቋቋም ከተፈናቃዮች ጋር ተደጋጋሚ ውይይት ሲደረግ መቆቱም ተመልክቷል፡፡            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም