ኢትዮጵያን በድሮን ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

69

ጥር 6/2013 (ኢዜአ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ኢትዮጵያን በድሮን ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎች የጋራ አቅም መገንቢያና የእርስበርስ ማስተዋወቂያ መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎችን ጨምሮ በሀገር ውስጥ የድሮን ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ኩባንያዎች ተሳትፈዋል።

በመድረኩ ላይ ኩባንያዎቹ ያላቸውን ተቋማዊ አቅም፣ የሚሰጡትን አገልግሎትና አጀማመራቸውን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።   

ኤን-ጄት ፣ ደጀን አቬሽን ኢንዱስትሪ፣ አቮን ፣ኢትዮ-ሬድ ፎክስ አግሪካልቸር ስፕራይንግ ድሮን ካምፓኒ፣ ፋሪስ እና ማይሻ የተባሉ ተቋማት በተወካዮቻቸው በኩል ገለጻ አድርገዋል።

ከዚህ በፊት በድሮን ቴክኖሎጂ በጋራ ለመስራት የሚያስችል መደላድል እንዳልነበር አስታውሰው መድረኩ በቀጣይም በትብብር ለመመስረት፣ አቅምን ለማጎልበትና የእውቀት ሽግግር ለማድረግ እንደሚረዳቸው አንስተዋል።

የደጀን አቬየሽን ኢንዱስትሪ ስራ እስኪያጅ ሌተናል ኮሎኔል አገሬ ተሰማ እንደተናገሩት መድረኩ የድሮን ቴክኖሎጂን በአገር ውስጥ ለማበልጸግ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው ።

ኩባንያዎቹ ለጋራ አላማ በአንድ መድረክ መምከራቸው  የድሮን ቴክኖሎጂ ትሩፋቶችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ተጠቃሚ ለመሆን ያስችላል ብለዋል።

“የመድረኩ መፈጠር በዘርፉ የተሰማሩ የግል ኩባንያዎችን አቅም ለመገንባት ከማስቻሉም በላይ ከህግና ከፋይናንስ አኳያ ያሉብን ችግሮች እንዲፈቱልን ይረዳል” ብለዋል።

በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎች ለአገር እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ መንግስት ተመሳሳይ መድረኮችን መፍጠር ይኖርበታል ነው ያሉት።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ያኒያ ሰይድመኪ በበኩላቸው “መድረኩ የትኛው ኩባንያ ምን አቅም እንዳለው፤ በምን ዘርፍ ቢሳተፍ ውጤታማ እንደሚሆን ለመለየት አስችሎናል” ብለዋል።

መሰል ቴክኖሎጂዎችን አሟጦ መጠቀም አገራዊ እድገትን ለማገዝ አስፈላጊ በመሆኑ በቀጣይም ተተኪዎችን ለማፍራት በሰው ሃብት ግንባታ ላይ እንዲያተኩሩ አሳስበዋል።

የዘርፉን ኩባንያዎች የጋራ አቅም መገንቢያና የልምድ መለዋወጫ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት በ10 ዓመት ተቋማዊ ስትራቴጂክ እቅድ ውስጥ መካተቱንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያን በድሮን ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑም ተናግረዋለ። 

ሚኒስቴሩ በሰው ሃብት ግንባታ፣ በቴክኖሎጂና በልምድ ልውውጥ በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን የጋራ ስምምነት ከኩባንያዎቹ ጋር ተፈራርሟል።

አሁን ላይ አገራት የድሮን ቴክኖሎጂን ለአገልግሎት ዘርፍ፣ ለውትድርና ተልዕኮ፣ ለህክምና፣ ለግብርና እና ሌሎችም መስኮች እየተጠቀሙበት መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም