በደቡብና በኦሮሚያ ክልሎች የ13 ወረዳዎች ነዋሪዎች የቢጫ ወባ ክትባት ተከትበዋል

58

ጥር 6/2013 (ኢዜአ) በደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች የ13 ወረዳዎች ሁሉም ነዋሪዎች በቢጫ ወባ የክትባት ዘመቻ መከተባቸውን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለፀ።

ክትባቱ በሁለቱ ክልሎች ለሚገኙ ከ700 ሺህ በላይ ነዋሪዎች መሰጠቱ ነው የተገለጸው።

በደቡብ ክልል በየካቲት 2012 ዓ.ም የቢጫ ወባ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ 86 ሰዎች በበሽታው መያዛቸውና አራት ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ ይታወቃል።

የወረርሽኙን መከሰት ተከትሎ በክልሉ 11 ወረዳዎችና በኦሮሚያ ክልል አጎራባች በሚገኝ አንድ ወረዳ ለሚኖሩ 704 ሺህ ሰዎች ክትባት ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ኢንስቲትዩቱ መግለፁም ይታወሳል።

የቢጫ ወባ የክትባት ዘመቻን አስመልክቶ አናዶሉ የዜና ወኪል የዓለም ጤና ድርጅትን መረጃ ዋቢ አድርጎ ከሁለት ቀናት በፊት ባወጣው ዘገባ በዘመቻው 93 በመቶ ስኬት መመዝገቡን አስነብቧል።

ዘመቻውን አስመልክቶ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የበሽታዎች ቅኝትና ምላሽ ዳይሬክተር አቶ መስፍን ወሰን ለኢዜአ እንደገለፁት በዘመቻው በሁለቱ ክልሎች በሚገኙ 13 ወረዳዎች የሚኖሩ 702 ሺህ 906 ሰዎች የቢጫ ወባ ክትባት ተከትበዋል።

ክትባቱ 14 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበትና ከጥቅምት 13 እስከ 19 ቀን 2013 ዓ.ም መሰጠቱንም ገልፀዋል።  

በዘመቻው በ13ቱ ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎች በሙሉ መከተባቸውንና በዕቅዱና በአፈፃፀሙ ልዩነት የተፈጠረው በአካባቢው እንደሚኖሩ የተተነበየውና አሁን የሚኖሩት ሰዎች ቁጥር በመለያየቱ መሆኑን አስረድተዋል።

ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በተገኘው የሕዝብ ቁጥር ትንበያ መሰረት ዕቅዱ መታቀዱ ልዩነት መፍጠሩን ጠቁመዋል።

የቢጫ ወባ ቫይረስ በሽታ በትንኝ ንክሻ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ሲሆን ምልክቶቹም ትኩሳት፣ የጡንቻና የወገብ ሕመም፣ የራስ ምታት፣ ማቅለሽለሽና ማስታወክ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም