የመዲናዋ የመሬት ይዞታ አስተዳደር ጽህፈት ቤት የበጀት አመቱ ስድስት ወራት የገቢ አፈፃፀም ከእቅዱ 15 በመቶ ብቻ ነው

58

ጥር 6/2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ይዞታ አስተዳደር ጽህፈት ቤት የበጀት አመቱ ስድስት ወራት የገቢ አፈፃፀሙ ከእቅዱ 15 በመቶ ብቻ መሆኑ ተገለጸ።

ጽህፈት ቤቱ የ2013 ግማሽ በጀት ዓመት አፈጻጸሙን ዛሬ የገመገመ ሲሆን ክንውኑም ዝቅተኛ መሆኑ ተገልጿል።

ለአፈፃፀሙ ዝቅተኛ መሆን ዋነኛው ምክንያት የመሬት ይዞታ ስራ ለአራት ወራት በመቋረጡ መሆኑም ታውቋል።

አገልገሎቱ ተቋርጦ የነበረው ከመሬት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመለየትና ችግሩን ለመፍታት ታስቦ መሆኑ በውይይቱ ላይ ተነስቷል።

በዚህም የይካተተልኝ አገልግሎት፣ በመብት ፈጠራ ስራ አዲስ ካርታ መስጠት፣ የካርታ ጀርባ ማህተምና ሌሎች ተያያዥ ስራዎች ተስተጓጎለው ቆይተዋል።

የጽህፈት ቤቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተክሉ ቤያሞ እንደገለጹት በሁለተኛው ግማሽ በጀት ዓመት የባለፈውን ጭምር የሚያካክስ ስራ ለማከናወን ዝግጅት ተደርጓል።

ካለፈው ወር አጋማሸ ጀምሮ አገልግሎት መስጠት መጀመሩንም ገልጸዋል።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ሃይሉ ማሞ በበኩላቸው መሬት በአግባቡ ከተያዘ የአገር ሀብት መሆኑን ገልጸው፣ የመዲናዋ የመሬት ከሃብት አጠቃቀም አኳያ ብዙዎች የሚንገላቱበትና የሚማረሩበት እንደሆነ ተናግረዋል።

ተገልጋዮች ለእንግልት የሚዳረጉትም ከአመራር ጀምሮ እስከ ባለሙያ ድረስ ባለ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ቁርጠኝነት ማነስ መሆኑን ገልጸዋል።

የጽህፈት ቤቱ ሰራተኞች የሚታዩ ክፍተቶችን ለማረም የአገልጋይነት ስሜታቸውን እንዲያሳድጉ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም