አትሌት ሙሉ ሰቦቃ የዳሊያን ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድር አሸነፈች

133
አዲስ አበባ ግንቦት 5/2010 አትሌት ሙሉ ሰቦቃ ዛሬ ማለዳ በቻይና በተካሄደው የዳሊያን ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድር ድል ቀንቷታል። አትሌቷ ውድድሩን ለማጠናቀቅ 2 ሰዓት ከ28 ደቂቃ ከ59 ሴኮንድ ፈጅቶባታል። የገባችበት ጊዜ እ.አ.አ በ2015 በዱባይ ማራቶን 2 ሰዓት ከ21 ደቂቃ ከ56 ሴኮንድ በመግባት በርቀቱ ካስመዘገበችው የግል ምርጥ ሰዓቷ በመቀጠል ሁለተኛው ፈጣን ሰዓቷ ነው። አትሌት ሙሉ በቻይና ከተሞች በሚካሄዱ የማራቶን ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ጥሩ ልምድ ያላት ሲሆን ባለፈው ዓመት በሼንዘን ማራቶን ሁለተኛ መውጣቷ የሚታወስ ነው። የባለፈው ዓመት የውድድሩ አሸናፊ ኬንያዊቷ ኤድናህ ሙክዋናህ 2 ሰዓት ከ32 ደቂቃ ከስድስት ሴኮንድ ሁለተኛ ስትወጣ ሌላኛዋ ኬንያዊት ሮዳህ ጄፕኮሪር 2 ሰዓት ከ32 ደቂቃ ከ53 ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች። በወንዶች ኬንያዊው ኤድዊን ኪቤት ኮኤች 2 ሰዓት ከዘጠኝ ደቂቃ ከ44 ሴኮንድ በመግባት እ.አ.አ በ2012 በኬንያዊው ጁሊየስ ማይሴይ ተይዞ የነበረውን የቦታውን ክብረ ወሰን በ44 ሴኮንድ አሻሽሎታል። የባለፈው ዓመት የውድድሩ አሸናፊ ኬንያዊው ዊሊያም ኒግሌል 2 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ከ31 ሴኮንድ ሁለተኛ ሲወጣ፤ ኢትዮጵያዊው ሀብታሙ ወጊ 2 ሰዓት ከ12 ደቂቃ ከ17 ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። በሁለቱም ጾታዎች ያሸነፉት ተወዳዳሪዎች የ30 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ሽልማት አግኝተዋል። ለ31ኛ ጊዜ የተካሄደው የዳሊያን ዓለም አቀፍ ማራቶን በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር(ፊፋ) የነሐስ ደረጃ የተሰጠው ውድድር ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም