ኢትዮጵያ በክህሎትና በመልካም ስነ-ምግባር የታነጸ ቅን ሰራተኛ ያስፈልጋታል - የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር

81

ፍቼ  ጥር 6/2013 (ኢዜአ) ፈርጀ ብዙና ፈታኝ ችግሮችን እያለፈች ያለችው ኢትዮጵያ በክህሎትና በመልካም ስነ-ምግባር የታነጸ ቅን ሰራተኛ ያስፈልጋታል ሲሉ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ገለጹ።

ከአራተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የሆነው ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ 1ሺህ 266 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።

ሚኒስትሩ በምረቃት ስነ ስርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ የቀን አቆጣጠር፣ የራሷ ፊደልና እንደ ገዳ ያሉ የጥንት የአስተዳደር ስርዓት ያላት አገር መሆኗን አውስተዋል።

“ይህም ሆኖ አሁን ከውስጥም ይሁን ከውጭ የሚገጥሙ  ችግሮችን እያለፈች ተገኛለች” ብለዋል።

“እነዚህን ችግሮች አልፋ የብልጽግና ጉዞዋን እንድታሳካ ታዲያ በክህሎትና ስነ-ምግባር የታነጹ ቅንና ታታሪ ሰራተኞች ያስፈልጓታል” ብለዋል።

ሚኒስቴ መስሪያ ቤታቸውም የዚህ ዓይነቱን ትውልድ ለመፍጠር ተግቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በኮቪድ 19 ተፅዕኖ ምክንያት የተቋረጠውን የገጽ ለገጽ ትምህርት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ በግል ስራና ንባብ እንዲሁም በልዩ ልዩ ፈጠራዎች ወደ መልካም አጋጣሚ ቀይረው መጠቀማቸውን እንደ አብነት አንስተዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ገናናው ጎፌ በበኩላቸው ተማሪዎች አንዱን የትምህርት ገበታ አገባዳችሁ ወደ አዲሱ ምዕራፍ እየገቡ እንደመሆናቸው እራሳቸውን ለዚህ ዝግጁ እንዲያደርጉ መክረዋል።

“አዲሱ ምዕራፍም ያስተማሯችሁን ወላጆችና አገራችሁን በቅንነት የምታገለግሉበት እና አምባሳደር የምትሆኑበት እንዲሆን እመኛለሁ” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ከአግሮ ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል 3.93 ነጥብ በማምጣት በከፍተኛ ማእረግ የተመረቀችው ተማሪ መገርቱ ጉደታ እንዳለችው ምንም እንኳን ተግዳሮቶች ቢኖሩም ለፍጻሜ ማድረስ ይገባል።

የተፈጥሮ ሀብት ክፍለ ትምህርት 3.99 በማምጣት በወርቅ ሜዳሊያ የተመረቀው ተማሪ ስመኘው አወቀም እኛ በዓላማ ተመስርተን ከስኬት መድረሳችን ለሌሎች ተማሪዎች ጥሩ ምሳሌ ይሆናል” ብለሏል።

በ5 ኮሌጆችና 17 የትምህርት ክፍሎች 1ሺህ 266 ተማሪዎችን በመጀመሪያ ዲግሪ ያስመረቀው ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ውጤት ላመጡ 15 ሴት ተማሪዎች በራሱ ግቢ የትምህርትና የስራ ዕድል አመቻችቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም