ኦስትሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ትሰራለች - አሌክሳንደር ሻለንበርግ

76

ጥር 6/2013 (ኢዜአ) ኦስትሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር እንደምትሰራ የኦስትሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ሻለንበርግ ገለጹ።

ኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ጉዳያቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱም ጠይቀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን  የኦስትሪያውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ሻለንበርግ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለኦስትሪያ አቻቸው በትግራይ ክልል ስለተወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ፣የኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ጉዳይና የሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ዙሪያ ማብራሪያ መስጠታቸውን ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር እርምጃው ተጠናቆ "ወንጀሎችን የማደንና መልሶ ማቋቋም" ምዕራፍ መሸጋገሩን መግለጻቸውንም ነው የተናገሩት።

መንግስት  ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባባር በክልሉ ለሚገኙ ዜጎች አስፈላጊው የሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ለኦስትሪያ አቻቸው ማብራሪያ እንደሰጧቸውም አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገልጸዋል ።

የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን በመጠገን ወደ አገልግሎት እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያና የሱዳን ረጅም ጊዜ የቆየ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው በማንሳት በተፈጠረው ሁኔታ ኢትዮጵያ ማዘኗን መግለጻቸውን ነው አምባሳደር ዲና ያብራሩት።

ኢትዮጵያ የድንበሩ ጉዳይ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈታ ጽኑ ፍላጎት እንዳላትና ጉዳዩን ለመፍታት የተጀመረው የዲፕሎማሲ ጥረት እንደሚቀጥልም አመልክተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ኢትዮጵያ ከሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር ተያይዞ የታችኛውን ተፋሰስ አገራት የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት መግለጻቸውንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የወንዙን አብዛኛው ድርሻ እንደምታበረክትና በድርድሩም ውሃውን በፍትሃዊነትና በእኩልነት የመጠቀም መርህ እንደምታንጸባርቅም አንስተዋል።

የኦስትሪያውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ሻለንበርግ  በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ሰላምና መረጋጋት ያላትን ሚና ሀገራቸው እንደምትገነዘብ መግለጻቸውን ተናግረዋል።

ከትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያዘዘ የሕግ ማስከበር እርምጃው በተሳካ ሁኔታ በመጠናቀቁ ደስታቸውን እንደገለጹም ነው አምባሳደር ዲና የጠቆሙት።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና የሶስትዮሽ የድንበር ጉዳይ በድርድር በሰላማዊ መንገድ መፈታት እንዳለበት ለኢትዮጵያ አቻችው እንደገለጹም አመልክተዋል።

በተጨማሪ ሁለቱ ሀገሮች ያላቸውን ትብብር ይበልጥ በሚያጠናክሩበት ጉዳዮች ላይ መምከራቸውንም ገልጸዋል።

ኦስትሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በግብርናና ኢነርጂ እንዲሁም በንግዱ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጎልበት እንደምትሰራ መግለጻቸውንም ተናግረዋል።

ኦስትሪያ በውሃ ሀብት አጠቃቀም ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያ ማካፈል እንደምትሻ መናገራቸውንም አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ጨምረው ገልጸዋል።

የኦስትሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ሻለንበርግ በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት የሚያደርጉ ሲሆን፤በቆይታቸው ከሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች ጋር ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ  ይጠበቃል።

የኦስትሪያ መራሔ መንግስት ሰባስቲያን ኩርዝ ከሁለት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም