ሀገር አቀፍ የዲያስፖራ ተሳትፎ ስትራቴጂ መቅረጽ የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈረመ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር አቀፍ የዲያስፖራ ተሳትፎ ስትራቴጂ መቅረጽ የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈረመ
ጥር 6/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ሀገር አቀፍ የዳያስፖራ ተሳትፎ ስትራቴጂ መቅረፅ የሚያስችል መግባቢያ ሰነድ ከአራት የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተፈራረመ።
ኤጀንሲው ስምምነቱን የተፈራረመው ከሐዋሳ፣ ጂግጂጋ፣ ወሎና ጅማ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ነው።
ስምምነቱ ሀገር አቀፍ የዲያስፖራ ተሳትፎ ስትራቴጂ ለመቅረፅ እንዲሁም ተሳትፎው ያለበትን ሁኔታና ያጋጠሙ ችግሮችን ላይ በጋር ጥናት ለማድረግ የሚያስችል ነው።
የዳያስፖራ ፖሊሲ የክለሳ ምክረ ሃሳብ ማዘጋጀትንም ያካትታል።
የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ እንዳሉት በስምምነቱ መሰረት ጥናቱን ለማድረግ ከዩኒቨርሲቲዎቹ የተውጣጡ 12 ተመራማሪዎችን የያዘ የቴክኒክ ጥናት ቡድን ይመሰረታል።
የፋይናንስና የአካሄድ ዝርዝር ጉዳዮችን በተመለከተ ቡድኑ በሚያቀርበው ዝርዝር ፕሮግራም መሰረት እንደሚከናወንም ተናግረዋል።
በቀጣይ የሚከናወኑ ዝርዝር ተግባራት በጥናቱ ቴክኒክ ቡድንና በኤጀንሲው አስተዳደራዊ ቡድን ይመራል ብለዋል።
የፖሊሲዎችና የስትራቴጂዎች ቀረፃ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ሙያዊ እገዛ ይሻሉ ያሉት ዶክተር መሐመድ፣ስምምነቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑበት ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
የጂግጂጋ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ኤልያስ አብዱላሂ ዩኒቨርሲታቸው በዳያስፖራ ተሳትፎ ላይ ከሚሰሩት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት ውጤት ለማምጣት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ የምርምና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ፋሪስ ሀይሉ በበኩላቸው ዩኒቨርሲታቸው በዳያስፖራ ተሳትፎ ያለውን ልምድ ተጠቅሞ ለስምምነቱ ውጤታማነት እንደሚያሰማራ ተናግረዋል።
ኤጀንሲውና ዩኒቨርሲቲዎቹ ላለፉት ሁለት ቀናት በአገር አቀፍ የዳያስፖራ ስትራቴጂ ቀረፃ፣የዳያስፖራ ተሳትፎ ያለበትን ሁኔታ የሚያሳይ ጥናትና በዳያስፖራ ፖሊሲ ላይ ውይይት አድርገዋል።