የገጠር ኢነርጂ ልማትና ማስፋፊያ ማዕከል አገልግሎት መስጠት ጀመረ

72

አዲስ አበባ፤ ጥር 6/2013(ኢዜአ) በአዲስ መልክ የተደራጀው የገጠር ኢነርጂ ልማትና ማስፋፊያ ማዕከል በይፋ ስራውን ጀመረ። 

ማዕከልሉ በ1994 ዓ.ም በአዋጅ ተቋቁሞ በገጠርና ከተማ ጥቅም ላይ የሚውሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን  ሲያመርት መቆየቱ ይታወሳል።

አሁን ላይ በአዲስ መልክ ተደራጅቶ ወደ ስራ የገባ ሲሆን፤ ወጪ ቆጣቢ የሆኑ ዘመናዊ ተክኖሎጂዎችን ተደራሽ በማድረግ የገጠሩን ማህበረተሰብ አኗኗር በመቀየር ረገድ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ተብሏል።

የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከጂኦ ተርማል፣ከፀሐይና ከውሃ ኃይል 4ሺህ 500 ሜጋ ዋት ኃይል እንደሚመነጭ ተናግረዋል።

በቀጣዮቹ ዓመታት ይህን ሃይል ወደ 20 ሺህ ሜጋ ዋት ከፍ ለማድረግ እቅድ መያዙንም ገልጸው በአሁኑ ወቅት በገጠር አካባቢ ከሚኖሩ ዜጎች መካከል አብዛኛው የኤሌክትሪክ ሃይል እንደማያገኝ ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በዚህ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች የሃይል ፍላጎታቸውን ለማሟላት የማገዶ እንጨት፣ከሰልና ከግብርና ተረፈ ምርቶችን ይጠቀማሉ ብለዋል።

የማዕከሉ ወደ ስራ መግባት መንግስት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ያለውን የሃይል ተደራሽነት ለማሻሻል የሚያደርገውን ጥረት በማገዝ ረገድ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።

የማዕከሉ ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ሚካኤል ገሰሰ በበኩላቸው ማዕከሉ ወጪ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን በተለየ አቀራረብ ተደራሽ ለማድረግ በአዲስ መልክ መደራጀቱን ተናግረዋል።

ከጸሃይ፣ከንፋስና ከውሃ እንዲሁም ከባዮ ማስ ሃይል አመንጭቶ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራም ጨምረው ገልጸዋል።   

ማዕከሉ ከጀርመኑ ጂ አይ ዜድ ጋር በመሆን ውሃን በመጠቀም  ሃይል የሚያመነጭ ቴክኖሎጂ በሙከራ ደረጃ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ማዕከሉ እስካሁን ባለው ሂደት 30 ሺህ የባዮ ጋዝ ማብለያዎችን በተለያዩ የገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍሎች ማሰራጨቱንም ገልጸዋል።  

ማዕከሉ በይፋ ስራው ከማስጀመር በተጓዳኝ ከጥር 6 እስከ 8 2013 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ የቴክኖሎጂ አውደ ርዕይ ተከፍቷል።

በአውደ ርዕዩ ላይ የሃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂና ሌሎችም ሃይል ማመንጫ ቴክኖሎጂዎች ለዕይታ ቀርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም