የዳያስፖራ ተሳትፎ ስትራቴጂ ለማዘጋጀትና የኢንቨስትመንት ተሳትፎውን ለማመላከት የሚያግዝ ጥናት ሊካሄድ ነው-ኤጀንሲው

50

አዲስ አበባ፤ ጥር 5/2013(ኢዜአ) በአገር አቀፍ ደረጃ የዳያስፖራ ተሳትፎ ስትራቴጂ ለማዘጋጀትና የዳያስፖራውን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማመላከት የሚያግዝ ጥናት ሊያካሂድ መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ጥናቱን ለማካሄድ ከሃዋሳ፣ ጂግጂጋ፣ ጅማ እና ወሎ ዩኒቨርሲቲዎች ተመራማሪዎችና ተወካዮች ጋር ውይይት እየተካሄደ ነው።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት እንዳሉት ዳያስፖራው ለአገራዊ ፕሮጀክቶችና ወቅታዊ ጥሪዎች ምላሽ እንዲሰጥና በኢንቨስትመንት እንዲሳተፍ የማስተባበር ሥራ እየሰራ ነው።

እየጨመረ የመጣውን የዳያስፖራውን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ፍላጎት የማስተናገድ አቅም በተመለከተ ባለፈው ዓመት የመነሻ ዳሰሳ ጥናት መካሄዱንም አስታውሰዋል።  

በውይይቱ የተሳተፉ ዩኒቨርሲቲዎች በሚገኙባቸው ክልሎች በዳያስፖራ ተሳትፎ ላይ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወኑ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

መድረኩ ኤጀንሲው ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር በአገር አቀፍ ደረጃ የዳያስፖራውን ተሳትፎ ማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ለሚደረገው ጥናት ስምምነት ላይ ለመድረስ እንደሚያግዝ ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።

ጥናቱ በአገሪቷ የዳያስፖራ ተሳትፎ ስትራቴጂ ለማዘጋጀትና ለስምንት ዓመታት እያገለገለ ያለውን የዳያስፖራ ፖሊሲ ወቅቱ በሚፈልገው መልኩ ለመቃኘት የሚረዳ መሆኑንም አስረድተዋል።

በጥናቱ የሚሳተፉት የዩኒቨርሲቲዎች ተወካዮች በበኩላቸው ከዚህ ቀደም የዳያስፖራውን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችሉ ጥናቶችና የትብብር ስራዎችን ሲያካሂዱ መቆየታቸውን አውስተዋል።

በመድረኩ እንደተገለፀው ጥናቱ አገራዊ የዳያስፖራ ተሳትፎ ስትራቴጂ ለማዘጋጀት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የዳያስፖራ የኢንቨስትመንት ተሳትፎና የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ያለበትን ሁኔታ እንዲሁም ያጋጠሙ ችግሮችና ክፍተቶችን ለማጥናት የሚረዳ ነው።

በዛሬው የውይይት መድረክ የኤጀንሲው አጠቃላይ ሁኔታ፣ የጥናቱን ዓላማ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲዎች ያካሄዱት የዳያስፖራ ተሳትፎ ስትራቴጂ ጥናት እና ሌሎች ሰነዶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ነገ በሚካሄደው መድረክ በቀጣይ ለሚደረገው ጥናት ኤጀንሲው ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የጋራ መግባቢያ ሰነድ ስምምነት ከማድረግ ባለፈ የአገር አቀፍ የጥናት ቡድኑ በይፋ ይመሰረታል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም