የጸረሙስና ትግሉን ውጤታማ ለማድረግ ተቋማዊ አቅም ማጠናከር ይገባል

136

አዲስ አበባ፤ ጥር 5/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የጸረሙስና ትግሉን ውጤታማ ለማድረግ ተቋማዊ አቅምን ማጠናከር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተጠቆመ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅን እንደገና ለማሻሻል የወጣ ረቂቅ አዋጅ ላይ የአስረጅ መድረክ አካሂዷል።

በኢትዮጵያ የልማት፣ የሠላምና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን በማፋጠን ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ ሙስናና ብልሹ አሰራርን መከላከል አስፈላጊ በመሆኑ ኮሚሽኑን እንደገና ማቋቋም ማስፈለጉ በረቂቁ ተገልጿል።

ኮሚሽኑ አገራዊ የጸረ-ሙስና ፖሊሲና ስትራቴጂ ማዘጋጀት፣ የህዝብ ተመራጮችን፣ የመንግስት ተሿሚዎችን፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶችንና የሌሎችን ሃብት መመዝገብና ማሳወቅ ከተግባራቱ መካከል ይጠቀሳሉ።

በመድረኩ የተገኙ የቋሚ ኮሚቴው አባላት፣ ሲቪል ማህበራትና የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ተወካዮች በረቂቅ አዋጁ የተደነገጉና በድጋሚ መታየት ያለባቸውን ሃሳቦች ዘርዝረዋል።

በዚህም በማቋቋሚያ አዋጁ በተዘረዘሩ የኮሚሽኑ ስልጣንና ተግባራት፣ አደረጃጀት፣ የአሰራር ነጻነት፣ አሻሚ የሆኑና ለትርጉም የተጋለጡ ድንጋጌዎች ላይ በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበዋል።

ኮሚሽኑ ሲቋቋም በተሟላ ግብዓት ተደራጅቶ የነበረ ቢሆንም እየተንሰራፋ የመጣው የመልካም አስተዳደር ችግርና የባለስልጣናት በሙስና መዘፈቅ ተግባሩን በነጻነት እንዳያከናውን ማድረጉም ተገልጿል።

ካለፈው በመማር በተለያዩ ደረጃዎች ህዝብ የሚያማርሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ኮሚሽኑን ድጋሚ በማቋቋም በአዋጅ ስልጣን መስጠት ብቻውን በቂ እንዳልሆነም ተሳታፊዎቹ አንስተዋል።

በመሆኑም የኮሚሽኑ አሰራር የግልጽነትና ተጠያቂነት መርሆችን ተከትሎ የአገርን ሃብት ከምዝበራ እንዲታደግ በሰለጠነ የሰው ኃይል፣ በግብዓትና በሌሎችም ማጠናከር እንደሚያስፈልገ ነው የተገለጸው።

ተቋሙ እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ ሲያከናውን የነበረውንና የተነጠቀውን የሙስና ምርመራና ክስ ማቅረብ ተግባር ረቂቅ አዋጁ ሊያካትተው እንደሚገባም ተነስቷል።

ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ተስፋዬ ዳባ በበኩላቸው በሙስና የተገኘን ሃብት ለማስመለስ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በርካታ ድርጅቶችን እየመረመረ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

"በመሆኑም በጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የተያዙ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ሳይጠናቀቁ ወደ ኮሚሽኑ ማዛወር ክፍተት ሊፈጥር ይችላል" ብለዋል።

የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ምክትል ኮሚሽነር ወዶ አጦ የተሰጡ አስተያየቶች በረቂቅ አዋጁ በድጋሚ እንደሚታዩ ገልፀዋል።

ኮሚሽኑ የተሰጠው ስልጣን ትልቅ ቢሆንም በአመለካከትና በተግባር ተሽመድምዶ እንዲዳከም መደረጉን አስታውሰው መጠናከሩ አስፈላጊ መሆኑን በአጽዕኖት አንስተዋል።

የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲሆን የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የራሳቸውን ኮሚሽን እንደሚያቋቁሙ ረቂቅ አዋጁ ደንግጓል።

ረቂቅ የማቋቋሚያ አዋጁ በመድረኩ የተነሱ ሃሳቦች ተካተውበት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም