የአፍና አፍንጫ ጭንብል በአግባቡ በመልበስ የኮሮና ቫይረስን መከላከል እንደሚገባ ከበሽታው ያገገሙ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ተናገሩ

74

ድሬዳዋ ፤ ጥር 5/2013 (ኢዜአ) የአፍና አፍንጫ ጭንብል በአግባቡ በመልበስ በበሽታው ምክንያት ሊደርስ የሚችልን ጉዳት አስቀድሞ መከላከል እንደሚገባ በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ያገገሙ የድሬደዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።

"እንድናገለግልዎ ማስክዎን ይልበሱ" መሪ ሃሳብ የንቅናቄ ዘመቻ ዛሬ በድሬዳዋ በይፋ ተጀምሯል፡፡

የንቅናቄው ዘመቻው ሲጀመር ከተገኙት የድሬዳዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ፍሬህይወት ደስታ በሰጡት አስተያየት በኮሮና ቫይረስ ተይዘው በህክምና እርዳታ ማገገም እንደቻሉ ገልጸዋል።

"ለ42 ቀናት በጽኑ ህሙማን ክፍል በነበርኩበት ወቅት ሶስት ልጆቼን ለማን በትኜ ልሞት ነው እያልሁ ተሰቃይቻለሁ›› ብለዋል።

ሌሎች ነዋሪዎች እሳቸው ገጥሟቸው ከነበረው ችግር በመማር ጭንብል በመልበስ ራሳቸውን ፣ ቤተሰባቸውንና ሀገራቸው ከኮሮና ስጋት መከላከል እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

ወጣት ገበየሁ ደርቤ በበኩሉ በተመሣሣይ በኮሮና ቫይረስ ተይዞ ለ29 ቀናት በኦክስጂን ሲተነፍስ እንደነበር አስታውሷል።

እንደ ሀገር ሆነ በድሬዳዋ ጭንብል ሣይለብስ አገልግሎት መስጠት የሚከለክለው ንቅናቄ መጀመሩ የተሻለ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ገልጿል፡፡

ከህመሙ እንደማልድን ተስፋ በቆረጥኩበት ወቅት የህክምና ባለሙያዎች ያደረጉልኝ ቅንና ሙያዊ ዕገዛ ህይወቴ እንዲተርፍ ወሳኝ አስተዋጽኦ አድርጎልኛል ብሏል፡፡

የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣና የህክምና ባለሙያዎችን ጫና ለመቀነስ ሁሉም የአፍንና የአፍንጫ ጭንብል በመልበስ ለዘመቻው መሳካት የድርሻውን እንዲወጣም መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር የጤና ቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ለምለም በዛብህ በወቅቱ እንዳሉት የአፍና አፍንጫ ጭንብል በመልበስ 85 በመቶ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ቢቻልም በአስተዳደሩ ጭንብልን የሚጠቀሙ የህብረተሰብ ክፍሎች እምብዛም ናቸው፡፡

በሁሉም መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጭምር የሚስተዋለው ይሄው ችግር ለመፍታት ዘመቻው መሰረታዊ ለውጥ ያመጣል ብለዋል፡፡

"ቫይረሱን መከላከል እየቻልን ዋጋ መክፈል የለብንም" ያሉት ኃላፊዋ ዘመቻው ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ጭንብል ሣይለብሱ አገልግሎት በሚሰጡት ተቋማት ላይ ክትትል በማድረግ እርምጃ እንደሚወሰድም አስታውቀዋል፡፡

ዘመቻውን በይፋ ያስጀመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሀመድ በበኩላቸው ቸልተኝነት ብዙ ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዘመቻው ስኬት በየደረጃው የሚገኘው አመራር በተግባር የታገዘ ግንባር ቀደም ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

"እንድናገለግልዎ ማስክዎን ይልበሱ " በሚል የተጀመረው የንቅናቄ ዘመቻ ለውጥ እንዲያመጣ ሁሉም በየተሰማራበት የሥራ መስክ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘመቻው በተጀመረበት ሥነ-ሥርዓት የመንግስት ሥራ ሃላፊዎች ፣የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉ ሲሆን ለዘመቻው መሳካት ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ቃል መግባታቸውን ሪፖርተራችን ከድሬዳዋ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም