የቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ትናንት ተካሄደዋል

126
አዲስ አበባ ግንቦት 5/2010 የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የ2010ዓ.ም የሁለተኛ ዙር ሶስተኛ ጨዋታዎች ትናንት በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ተካሄደዋል። በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም በተደረጉ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት የካ ክፍለ ከተማን 76 ለ 34 በሆነ ሰፊ ውጤት ሲያሸንፍ፤ ወልቂጤ ከተማ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን 76 ለ 61 ማሸነፍ ችሏል። በክልል ከተሞች ድሬዳዋ ላይ አዳማ ከተማ ድሬዳዋ ከተማን 43 ለ 41 ያሸነፈ ሲሆን፤ ሁለቱ ቡድኖች የተሸናነፉበት የነጥብ ልዩነት ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር እንደተደረገበት የሚያመላክት ነው። ጎንደር ላይ ሀዋሳ ከተማ ጎንደር ከተማን 58 ለ 43 ረቷል። የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ስምንት ቡድኖች የሚሳተፉበት ውድድር ነው። የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ የሴቶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግም ትናንት በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም በተደረገ አንድ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን 43 ለ 35 አሸንፏል። በዚህ ሳምንት በወጣው መርሃ-ግብር የፌዴራል መንግስት ቤቶች ኮርፖሬሽን ከአማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን ጨዋታቸውን ማድረግ የነበረባቸው ቢሆንም የፌዴራል መንግስት ቤቶች ኮርፖሬሽን ከውድድሩ ውጭ በመሆኑ ጨዋታው አልተካሄደም። የፌዴራል መንግስት ቤቶች ኮርፖሬሽን ያለፉትን ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ሳይጫወት በመቅረቱ ፎርፌ የተሰጠበት በመሆኑ በህጉ መሰረት "በሁለት ተከታታይ ጨዋታ ፎርፌ የተሰጠበት ቡድን ከውድድሩ ውጭ ይሆናል" ስለሚል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከሊጉ ተሰናብቷል። በዚህም ምክንያት አምስት ቡድኖች ይሳተፉበት የነበረው የኢትዮጵያ የሴቶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ወደ አራት ዝቅ ያለ ሲሆን፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ወልቂጤ ከተማ፣ አማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን እና ጎንደር ከተማ የሊጉ ተሳታፊ ክለቦች ናቸው። በሁለቱም ጾታዎች የሚካሄደው የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የተጀመረው በ2006ዓ.ም ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም