''እንድናገለግልዎ ማስክ ያድርጉ" የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከል ንቅናቄ ተጀመረ

45

አዲስ አበባ ጥር 5/2013 (ኢዜአ) ''እንድናገለግልዎ ማስክ ያድርጉ" በሚል መሪ ሃሳብ ለስድስት ወራት የሚቆይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን የመከላከል ንቅናቄ ተጀመረ።

በኮቪድ ወረርሽኝ ከተያዘው ሰው 56 በመቶውን የሚሸፍነው ቁጥር ከአዲስ አበባ መሆኑ ተገልጿል።

በአዲስ አበባ የኮቪድ ወረርሽኝ የመከላከል ቀጣይ ዕቅድና የመከላከያ ዘዴዎች አተገባበርን ለማጠናከር ለ6 ወራት የሚቆይ ንቅናቄ በከተማ አስተዳደሩና በጤና ቢሮ ትብብር ተጀምሯል።

ንቅናቄው "እንድናገለግልዎ ማስክ ያድርጉ" በሚል መሪ ሃሳብ እንደገና የመጠንቀቅ፣ እንደገና ማስክ የማድረግ ነው ተብሏል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ንቅናቄው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ መዘናጋት እየታየ በመሆኑ ዳግም ትኩረት በመስጠት የኮቪድ ወረርሽኝን ለመከላከል ነው ብለዋል።

ንቅናቄው ትኩረት የሚያደርገው ችግሩ በስፋት እየታየባቸው በሚገኙ ከተሞችና ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች እንደሆነም ጠቁመዋል።

ዓላማውም ማስክ ሳያደርጉ ባለመንቀሳቀስ የበሽታውን ስርጭት መግታት እንደሆነ ሚኒስትሯ ገልፀዋል።

በየዕለቱ በሚደረገው ምርመራ በመዲናዋ የበሽታው ስርጭት መጨመሩን ገልጸው ለ6 ወራት በሚካሄደው ኮቪድን የመከላከል ዘመቻ ርቀትን በመጠበቅና ማስክ በማድረግ ስርጭቱን እንግታ ሲሉ መልዕክታቸውን አተላልፈዋል።

አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ውሃና ሳሙና በየበራቸው ላይ በማስቀመጥ ቀደም ሲል ይደረግ የነበረውን ጥንቃቄ እንደገና በመጀመር ወረርሽኙን እንዲከላከሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የከተማዋ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ በቫይረሱ ከተያዘው የኅብረተሰብ ክፍል 56 በመቶው የሚገኘው በመዲናዋ መሆኑን ገልጸዋል።

እስካሁን በበሽታው የተያዙት 128 ሺህ ሰዎች ሲሆኑ ከሁለት ሺህ በላይ የሚሆኑት ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ወረርሽኙን ለመከላከል ይደረግ የነበረው ጥንቃቄ 75 በመቶ የነበረ ሲሆን አሁን ወደ 54 በመቶ መውረዱንና መዘናጋት በስፋት እየተስተዋለ መሆኑን ዶክተር ዮሐንስ ተናግረዋል።

በቅርቡ በተለያዩ የዓለም አገራት የተከሰተው አዲስ አይነት የኮሮና ቫይረስ የመሰራጨት አቅሙ ፈጣን በመሆኑ ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም