በጅግጅጋ 742 በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ደም ለገሱ

129
ጂግጂጋ ሀምሌ16/2010 በጎ ፍቃደኛ ወጣቶቹ በለገሱት ደም የሰዎችን ህይዎት መታደግ መቻላቸው የህሊና እርካታ እንደፈጠረላቸው በጅግጅጋ ከተማ የሚገኙ ደም ለጋሾች ተናገሩ፡፡ በክልሉ ጤና ቢሮ የጅግጅጋ ደም ባንክ ቅጥር ግቢ በተዘጋጀው ፕሮግራም 742 በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ደም ለግሰዋል፡፡ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከተሳተፉ ወጣቶች መካከል ወጣት መሀመድ አህመድ እንደተናገረው የደም ልገሳው ህይዎትን የማዳን ተግባር በመሆኑ የመንፈስ እርካታ የሚሰጥ ነው። "እኔ በወጣትነት እድሜየ በተለያዩ የጤናና አደጋ ምክንያት ደም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ለመርዳት ነፃ የደም ልገሳ ፕሮግራም ላይ ተሳታፊ በመሆኔ ደስተኛ ነኝ" ብሏል። ሌላው ወጣት ከድር አብዲ በዘመቻው በመሳተፌ ወላድ እናቶች በወሊድ ወቅት ሊያጋጠማቸው የሚችለውን የደም እጥረት ለመቅረፍ የበኩሉን ድርሻ ለማበርከት በመቻሉ መደሰቱን ገልጿል፡፡ የክልሉ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወጣት አህመድ ኑር ሼክ መሐመድ እንደተናገረው ፌዴሬሽኑ ከክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር ከ750 ሺህ በላይ ወጣቶች በተለይዩ የበጉ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሳተፍ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። ወጣት በጎ ፍቃደኞች ነፃ የደም ልገሳ፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በከተሞች ጽዳት፣ በሰላምና ፀጥታ የህዝቡን ግንዛቤ በሚያሳድጉ ስራዎች እና ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከል ላይ ያተኮሩ ተግባራት እስከመጪው መስከረም መጀመሪያ ሳምንት እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል፡፡ በክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዲዋሰዕ አህመድ እንዳሉት በበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመሳተፍ ላይ ላሉት ወጣቶች ቀደም ሲል ስለበጎ ፍቃድ አገልግሎት ምንነት እና ጠቀሜታው ዙሪያ በጅግጅጋ፣ ቀብርደሀር እና ጎዴ ከተሞች ስልጠና ተሰጥቷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም