የተፋሰስ ልማት የህብረተሰቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ አግባብ ይከናወናል ... አቶ አገኘሁ ተሻገር

177

ባህርዳር፤ ጥር 05/2013(ኢዜአ) ተፋሰስን መሰረት ያደረገ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የህብረተሰቡን ዘላቂ የልማት ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ አግባብ ይከናወናል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።

የዘንድሮ የበጋ ወራት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በአማራ ክልል ደረጃ  በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ላይ አርማጭሆ ወረዳ ተጀምሯል።

በሥራው ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት የተገኙት ርዕሰ መስተዳደሩ እንደገለጹት የተጀመረው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በጥራትና ውጤታማነት የሚከናወን ይሆናል።

የላይ አርማጭሆ ወረዳ ህዝብ የተፈጥሮ ሃብት ልማት መስራት ብቻ ሳይሆን ከተፋሰስ ልማትም መጠቀም መጀመሩን ርዕሰ መስተዳድሩ ባደረጉት የመስክ ምልከታ  ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

በሁሉም የክልሉ አካባቢ ትናንት በንቅናቄ የተጀመረው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በስኬት  በማጠናቀቅ የህዝቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።

የተጀመሩ ተፈሳስን መሰረት ያደረጉ  የልማት ስራዎች በጥራትና ህዝቡን በሚጠቅም መልኩ እንዲጠናቀቅም በየደረጃው ያለው አመራርና ባለሙያ አርሶ አደሩን በቅርበት ሊደግፍ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሚከናወኑ  የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ልማት ስራዎችም በቀጣይ በስነ ህይወታዊ ዘዴ በማጠናከር በአረንጓዴ አሻራ የተጀመረውን የችግኝ ተከላ ሥራ አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል ብለዋል።

ከልማቱ በተጓኘ አሁን የተገኘው ሠላም ቀጣይነቱ እንዲረጋገጥ ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን ልንሰራ ይገባል ሲሉም ርዕስ መስተዳድሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በሥፍራው የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ በበኩላቸው በሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

እስካሁን በተከናወኑ ተፋሰስን መሰረት ያደረጉ  የልማት ስራዎች የአፈር መሸርሸር እንዲቀንስ፣ የከርሰ ምድር ውሃና የሰብል ምርታማነት እየጨመረ እንዲመጣ ማስቻሉንም ነው የገለጹት።  

በተለይም ዛሬ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ላይ አርማጭሆ ወረዳ በሹማራ ሎምዬ ቀበሌ የለማው ተፋሰስ የአፈር ክለትን በመከላከልና የውሃ ስርገት እንዲጨምር አድርጓል ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት በተፋሰሱ ውስጥ የሚገኙ አርሶ አደሮችም ቡና፣ አቦካዶ፣ ማንጎና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው አትክልቶችን በማልማት ተጠቃሚነታቸው በተግባር በመረጋገጡ በሞዴልነት ተወስዶ እንዲሰፋ ይደረጋል።

በለሙ  የተፋሰሶች  የማህበረሰብ አጠቃቀም ልማት አዋጅ ፀድቆ ስራ ላይ በመዋሉም በቀጣይ የሁሉንም እኩል ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጥ ገልጸው፤ የተመዘገበው ስኬት የአመራሩና የአርሶ አደሮች ውጤት በመሆኑ በቀጣይም ተግባሩ አጠናክሮ በመቀጠል ዘላቂ ልማት ማረጋገጥ ይገባል ሲሊም ነው አቶ ሳኒ የጠቀሱት።

የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ ከተጀመረ ወዲህ የወደመውን የደን ሃብት የመመለስ ጅምር ውጤት ታይቷል ያሉት ደግሞ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወርቁ ኃይለማርያም ናቸው።

በዚህም የለሙ ተፋሰሶችና በተራቆቱ አካባቢዎች የደን ልማቱን በማሳደግ የደን ሽፋኑ ከ4 ነጥብ አምስት በመቶ ወደ 13 በመቶ  ማሳደግ መቻሉን ገልፀዋል።

በዞኑ በለሙ ተፋሰሶች ከ78 ሺህ በላይ ወጣቶችና አርሶ አደሮች በንብ ማነብ እንዲሁም በመስኖ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የስራ ዕድል በመፍጠር እየተጠቀሙ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

 የአፈርና ውሃ ጥበቃ  ልማት ስራዎችን በማስቀጠል የህብረተሰቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ  እንደሚሰራም ገልጸዋል።

በክልሉ በዘንድሮው የበጋ ወራት ከ8 ሺህ 300 በሚበልጡ ተፋሰሶች ውስጥ ከ328 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ተገልጿል።

ባለፈው ዓመት በክልሉ በህብረተሰቡ ተሳትፎ ከ254 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት  የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራዎች መከናወናቸውን ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም