በየአመቱ በአማካይ ከ14 ሺህ በላይ እናቶች በወሊድና ከወሊድ ጋር በተገናኘ ህይወታቸውን ያጣሉ- ዶ/ር ሊያ ታደሰ

127

አዲስ አበባ፣ ጥር 4/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በየአመቱ በአማካይ ከ14 ሺህ በላይ እናቶች በወሊድና ከወሊድ ጋር በተገናኘ ችግር ህይወታቸውን እንደሚያጡ የጤና ሚንስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የጤናማ እናትነት አምባሳደር ሆና ተመርጣለች።

የጤናማ እናትነት ወር ዘመቻ ዘንድሮ በአለም አቀፍ ደረጃ ለ35ኛ ጊዜ በኢትዮያ ደግሞ ለ15ኛ ጊዜ ይከበራል።

የዘንድሮው ጤናማ እናትነት ወር ዘመቻ “በደም መፍሰስ ምክንያት እናት ለምን ትሙት?” በሚል መሪ ሃሳብ ተጀምሯል።

በአለም ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው እናቶች ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር በተያያዙ ችግሮች ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ።

ከእዚህ ውስጥም በዋናነት 50 በመቶ የሚሆኑት እናቶች የሚሞቱት በደም መፍሰስ ሳቢያ መሆኑ ይገለጻል።

ወደ ጤና ተቋማት ሄደው የማይወልዱ እናቶች መኖር፣ የመሰረተ ልማት እና የህክምና ግብዓቶች እጥረት እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች የስነ-ምግባር ችግር መኖርም በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው።

የጤና ሚንስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዘመቻ ማስጀመሪያው መርሀ-ግብር ላይ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ በርካታ ቁጥር ያላቸው እናቶች ከወሊድ እና ከወሊድ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ህይወታቸውን ያጣሉ።

በአገሪቱ ከዚህ ቀደም በነበሩ አመታት በአመት በአማካይ እስከ 30 ሺህ የሚደረሱ እናቶች ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር በተያያዙ ችግሮች ህይወታቸው ያልፍ እንደነበር ያስታውሳሉ። 

አሁንም በየዓመቱ በአማካይ ከ14 ሺህ በላይ እናቶች በወሊድና ከወሊድ ጋር በተገናኘ ችግር ህይወታቸውን እንደሚያጡ ይገልጻሉ።

እንደ ዶክተር ሊያ ገለጻ፤ በኢትዮጵያ ባለፉት 15 አመታት እንደ አገር የእናቶችን ሞት በ15 በመቶ መቀነስ ተችሏል።

በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም በርካታ እናቶች በግንዛቤ ክፍተት ምክንያት ወደ ጤና ተቋማት ሄደው ከመውለድ ይልቅ በቤት ውስጥ የመውለድ ልምድ ነበራቸው።

ይህ አሁን ላይ የቀነሰ ሲሆን ከ10 ዓመት በፊት 10 በመቶ ብቻ የሚሆኑ እናቶች ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ ይወልዱ የነበሩ ሲሆን አሁን ላይ 51 በመቶ የሚሆኑ እናቶች ወደ ጤና ተቋማት ሄደው እንድሚወልዱ ገልጸዋል።

ይሁንና በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶች ቁጥር የጨመረ ቢሆንም አሁንም ድረስ ግን ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ እናቶች አሁንም በቤት ውስጥ እንደሚወልዱ ገልጸው ይህም ከፍተኛ ስራ መስራት የሚጠይቅ መሆኑን ነው ዶክተር ሊያ የሚገልጹት።

በመሆኑም የሴቶችን እና የእናቶችን ጤና ለማሻሻልና ከወሊድ በኋላ በሚከሰት የደም መፍሰስ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን ቁጥር ለመቀነስ ሁሉም በትብብር ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

መንግስት አሁን በተጀመረው የሁለተኛው የጤናው ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ ጤናን በሁሉም ዘርፍ ማካተት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል ብለዋል።

በዚህ ረገድ ያለውን የጤና አገልግሎት በማሻሻል የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ከፍተኛ ጥረት ይደረጋልም ሲሉም ተናግረዋል። 

የሴቶችና ህጻናት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላፊ በበኩላቸው፤ የእናቶች ጉዳይ አጠቃላይ የህጻናት፣ የወጣቶች የህዝብና የአገር ጉዳይ ነው ብለዋል።

በመሆኑም በወሊድ ምክንያት የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ሁሉም በየድርሻው መረባረብ አለበት ብለዋል።

በመርሀ-ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ለሚቀጥሉት 2 ዓመታት የጤናማ እናትነት አምባሳደር ሆና ተመርጣለች።

ኮማንደር አትሌት ደራርቱ አገሪቱ በተለይም በገጠር ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች የጤና አገልግሎት፣ የመሰረተ ልማትና ሌሎችም የመሳሰሉ በርካታ ችግሮች ይገጥሟቸዋል ብላለች።

በመሆኑም በገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ሁሉም በየተሰማረበት መስክ ለማገልገል ማህበረሰባዊ ግዴታውን እንድወጣም ጥሪ አቅርባለች።

በኢትዮጵያ ዘንድሮ ለ15ኛ ጊዜ የሚከበረው የጤናማ የእናትነት ወር እስከ ጥር መጨረሻ ድረስ የሚከበር ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም