ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች ከአንድ ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

71

አዳማ፣ ጥር 04/2013( ኢዜአ) ባለፉት ስድስት ወራት ወደ ውጭ ከተላኩ የተለያዩ ምርቶች ከአንድ ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ የዘርፉን የግማሽ ዓመት አፈፃፀም ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ እየገመገመ ነው።


የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋናው አረጋ በግምገማው መድረክ እንዳሉት ገቢው ከተገኘባቸው ምርቶች መካከል ወደ ውጭ የተላኩ ቡና፣ ቅመማ ቅመም፣ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎች ይገኙበታል።

ከማዕድንና ኢንዱስትሪ ምርቶች የተገኘው የውጭ ምንዛሬ የተሻለ መሆኑም ተገልጿል።

የተገኘው ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም  ከ224 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር ብልጫ መገኘቱን አመልክተዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ የተሻለ አፈፃፀም ያለ ቢሆንም ሀገሪቱ  ከውጭ ለምታስገባው የተለያዩ ምርቶች በዓመት ከ19 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ እያወጣች ነው።

ሀገሪቱ  ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶች በዓመት የሚገኘው ከ3 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር መዝለል አልቻለም ፤ አሁን ያለውን አቅምና አፈጻጸም ይዘን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ማሳካት አንችልም ብለዋል።

በተለይም በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ተወዳዳሪ ለመሆንና የሀገሪቱን ጥቅም ለማስጠበቅ በወጭ ምርቶች ጥራትና ብዛት ላይ መስራት እንደሚገባ አምባሳደር ምስጋናው ተናግረዋል።

የግብርናና ማኑፋክቸሪንግ የኢንዱስትሪ ምርቶችን የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ማሳለፍ፣ የንግድና ግብይት ሥርዓትን ማዘመን፣ የተቋማት የቴክኖሎጂ አጠቃቀም አቅም ማጎልበት፣ ድጋፍና ክትትል ላይ በሙሉ አቅም መስራት ግብ ለማሳካት እንደሚረዳ ጠቅሰዋል።


በዚህም የመንግስት እጅ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ባለሃብቶች የሚያጋጥማቸውን ችግር በማቃለል  በተለይም የአቅርቦት፣ መሬትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት መሰል መድረኮች ጠቃሚ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የተሻለ የሚደግፍና ለዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጥሩ ሴክተሮች ልዩ ድጋፍ እንደሚሰጣቸውም ሚኒስትር ዴኤታው  አስታውቀዋል።

በግምገማው መድረክ የተጋበዙት የኦሮሚያ ክልል  ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው የወጭ ንግድ ማሳደግ ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ቁልፍ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም  የክልሉን የኢኮኖሚ ዘርፍ  ለማነቃቃት ሁሉን አቀፍ የግብይት ስርዓት ከማሻሻል ጀምሮ ዘርፉን  የማዘመን፣ ባለሃብቶችን የማበረታታትና አገልግሎቱን በኤሌክትሮኒክስ ለማመቻቸት  የሚያስችል ሥርዓት እየተዘረጋ መሆኑን ተናግረዋል ።

በተለይም የክልሉ መንግስት ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ላይ እየሰራ ካለው ሌላ  የወጭ ንግድን ለማሳደግ በርካታ አግሮ ኢንዱስትሪዎችን እየገነባ መሆኑን አመልክተዋል።

በተጨማሪ ለክልሉ ባለሃብቶች የመሬትና  የመሰረተ ልማት ግብዓቶችን እያቀረበ መሆኑንም አስረድተዋል።


በወጭ ንግድ የሚሳተፉ ባለሃብቶች  እየጨመሩ ቢሆንም የምርት ዕድገትና ጥራት በሚፈልገው መልኩ እያደገ አይደለም ያሉት ደግሞ የቡና ላኪ ባለሃብትና የመድረኩ ተሳታፊ አቶ ሰዒድ ዳምጠው ናቸው።

ባለሃብቱ በጥራትና ብዛት እንዲያመርትም መንግስት መደገፍና ማበረታታት እንዳለበት  ጠቁመዋል።

በመድረኩ  አምራችና ላኪ ባለሀብቶችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም