በሚቀጥሉት አስር ቀናት በአብዛኛው የአገሪቷ ክፍሎች ደረቃማ የአየር ሁኔታ ተጠናክሮ ይቀጥላል

70

አዲስ አበባ፣ ጥር 4/2013 (ኢዜአ) በአብዛኛው የአገሪቷ ክፍሎች እየታየ ያለው ደረቃማ የአየር ሁኔታ በሚቀጥሉት አስር ቀናት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ገለጸ። 

ይሁን እንጂ አንዳንድ የስምጥ ሸለቆና አዋሳኝ አካባቢዎች ደቡብ ምስራቅ፣ የመካከለኛውና የደቡብ ምዕራብ ስፍራዎች ለጥቂት ቀናት አነስተኛ ዝናብ ይኖራቸዋል።

በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት ለደመና መፈጠር መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ የሚቲዎሮሎጂ መረጃ መሰረት በመካከለኛና ሰሜን ምስራቅ እንዲሁም በደቡባዊ የኢትዮጵያ ክፍሎች ሊኖር እንደሚችል ይጠበቃል።

በአንዳንድ አካባቢዎች አንጻራዊ የደመና ሽፋን መጨመርና ቀላል መጠን ያለው ዝናብ በጥቂት አካባቢዎች ሊኖር እንደሚችል የትንበያ መረጃዎች ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ በሚቀጥሉት አስር ቀናት ከአማራ ክልል ሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች፣ አዲስ አበባ፣ ከኦሮሚያ ክልል ጅማና ምዕራብ አርሲ ዞኖች፣ ከደቡብ የከፋ፣ ዳውሮ፣ የጋሞ፣ ጎፋ፣ ጉራጌና ሐዲያ ዞኖች፣ ጥቂት የሲዳማ ክልል አካባቢዎች ላይ አነስተኛ ዝናብ ይኖራቸዋል።

ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው የተቀሩት የአገሪቷ ክፍሎች ደረቃማ ሆነው ይቆያሉ።

በሚቀጥሉት አስር ቀናት የበጋው ደረቃማ የእርጥበት ሁኔታ እንደሚያመዝን የሚጠበቅ ሲሆን ይህም ለመኸር ምርት ድህረ ምርት ስብሰባ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል።

በአንጻሩ ለቋሚ ሰብሎችም ሆነ ለሳርና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት አሉታዊ ጎን እንደሚኖረው ይጠበቃል።

በዚህም በሰሜን ምስራቅ፣ በመካከለኛውና በደቡብ ምስራቅ የአገሪቷ አካባቢዎች ለጥቂት ቀናት የሚቆይ መጠነኛ እርጥበት የሚያገኙ ሲሆን ይህም በአፈር ውስጥ እርጥበት ለማጎልበትና ለበልግ እርሻ አዎንታዊ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።

በአብዛኛው የተፋሰስ አካባቢዎች ደረቅና እርጥበት ያዘለ የአየር ሁኔታ እንደሚቀጥልም ይጠበቃል።

በላይኛውና በመካከለኛው ኦሞ ጊቤ፣ በስምጥ ሸለቆ፣ የመካከለኛው አባይ ምስራቃዊ ክፍሎች፣ በላይኛው አዋሽና ጥቂት የላይኛው ዋቢ ሸበሌ ተፋሰሶች ደረቅና ከፊል ደረቅ ሁኔታ እንደሚያገኙ ይጠበቃል።

ይህም ሁኔታ በውሃ ዘርፍ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ስለሚኖረው የውሃ ኃብትን ብክነት መጠበቅ እንደሚያስፈልግ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም