ዩኒቨርሲቲው የ2ኛ አመት ተማሪዎችን ተቀብሎ የማካካሻ ትምህርት መስጠት ጀመረ

87

ሰመራ፣ ጥር 4/2013 ዓም (ኢዜአ)- ሰመራ ዩኒቨርሲቲ ከ2ሺህ 700 በላይ የ2ኛ አመት ተማሪዎችን ተቀብሎ የማካካሻ ትምህርት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ። 

ዩኒቨርስቲው በትምህርት ሚኒስቴር የተቀመጠ የኮሮና መከላከል መመሪያ መሰረት በማድረግ ባለፈው ወር  ከ1ሺህ 800 በላይ ተመራቂ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ መሆኑ ይታወቃል ።

ባለፈው ቅዳሜና እሁድ ደግሞ ከ2ሺህ 700 በላይ የ2ኛ አመት ተማሪዎችን ተቀብሎ ከትላንት ጀምሮ የማካካሻ ትምህርት መስጠት ጀምሯል።

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አብዱረህማን ከድር ለኢዜአ እንደገለጹት ከክልሉና ከፌደራል ትራንስፖርት መስሪያ ቤቶች ጋር በመቀናጀት ለተማሪዎቹ የትራንስፖርት አቅርቦት በማመቻቸት አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

ተማሪዎቹ ወደ ዮኒቨርስቲው እንደገቡም እራሳቸውን ከኮሮና እየተከላከሉ ትምህርታቸውን መከታተል እንዲችሉ ሁኔታዎች የተመቻቹላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል፣ ሳኒታይዘርና  የመታጠቢያ ሳሙናዎች በነፍስ-ወከፍ  የቀረቡላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የማደሪና መመገቢያ እንዲሁም የመማሪያ ክፍሎች ኮሮናን እየተከላከሉ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማከናወን በሚያስችል መልኩ መዘጋጀታቸውንም አመልክተዋል።

በተቀመጠው የማካካሻ  የትምህርት መርሃ ግብር መሰረት የመማር-ማስተማር ሂደቱ መጀመሩን አስታውቀዋል።

የዩኒቨርስቲው የ2ኛ አመት የታሪክ ተማሪ  ይደርሳል እስከመቼ በሰጠው አስተያየት አምና በኮሮና ክሰተት የተቋረጠውን ትምህርት በተቀመጠው ሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ በትጋት ለመስራት መዘጋጀቱን ገልጿል።

"የተቋረጠው ትምህርት በመጀመሩ ደስተኛ ነኝ፤ በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ ትምህርቴን ተከታትዬ ውጤታማ ለመሆን ተዘጋጅቻለሁ " ያለችው ደግሞ ሌላዋ የሁለተኛ አመት የሶሺዎሎጂ ትምህርት ክፍል ተማሪ ዘይነብ ሁሴን ናት።

ዩኒቨርሲቲው የካቲት 2013 ዓ.ም መጀመሪያ ተማሪዎችን እንደሚያስመርቅ ታውቋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም