በመዲናዋ ለሚገኙ አርሶ አደሮች ዘላቂ ተጠቃሚነት እየሰራሁ ነው - የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን

88

ጥር 3/2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ አስተዳደር የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን በመዲናዋ ለሚገኙ አርሶ አደሮች ዘላቂ ተጠቃሚነት እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

ኮሚሽኑ በመዲናዋ ከሚገኙ አርሶ አደሮች ጋር ባካሄደው ውይይት ከአገራዊ ለውጡ በፊት በነበረው የአርሶ አደሮች ሁኔታና ለውጡ ባስገኛቸው ትሩፋቶች ላይ ገለጻ ተደርጓል።

የመዲናዋ የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽነር ባዩ ሽጉጤ አገራዊ ለውጡን ከማስቀጠል አንጻር አርሶ አደሮች የራሳቸውን ሚና እንዲወጡ ውይይት ማድረግ ማስፈለጉን ተናግረዋል።

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ ከዚህ ቀደም በመዲናዋ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች አርሶ አደሩን ያሳተፉ አልነበሩም።

ህወሓት አገሪቷን በበላይነት ሲመራ በነበረበት ጊዜ ሰዎች ላይ ሳይሆን መሬት ፍለጋ ላይ ማተኮር ይስተዋል እንደነበረም አንስተዋል።

በዚህም በልማት ምክንያት የተነሱ አርሶ አደሮች ለማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ-ልቦናዊ ችግሮች ተጋልጠው መቆየታቸውን ነው ኮሚሽነሩ ያስታወሱት።

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በመንግስት በኩል ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

በዚህም የአርሶ አደሩን ችግሮች ከማድመጥ ጀምሮ ለችግር የተጋለጡትን መልሶ የማቋቋም ሥራ መሰራቱን ጠቅሰዋል።

አርሶ አደሩ በስፋት ሲጠይቅ የነበረውን የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ እንዲያገኝ መደረጉ የለውጡ ትሩፋት መሆኑንም ጠቁመዋል።

ምንም ገቢ የሌላቸውን አርሶ አደሮች መሰረታዊ ፍጆታቸውን ከመሸፈን ባለፈ መጠለያ እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑንም ነው ኮሚሽነሩ የገለጹት።

በዚህ ስራ እስካሁን 22 ሺህ 915 አርሶ አደሮች በከተማዋ ከተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን አብራርተዋል።

ኮሚሽነር ባዩ እንዳሉት በቀጣይም አርሶ አደሩ የችግሩ ባለቤት ብቻ ሳይሆን ችግር ፈቺ እንዲሆን ፕሮጀክቶች ተዘጋጅተው ወደሥራ ተገብቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም