የመተከል ዞን አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመተከል ዞን አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 3/2013(ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመተከል ዞንና ወረዳ ነባርና አዳዲስ አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው።
ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊ፣ አገራዊና ክልላዊ ይዘቶች ያሉትና በቪዲዮ ተቀርፆ የቀረበው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መልእክትም ለሰልጣኞቹ ቀርቧል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብልፅግና ፓርቲ የስልጠና እና ሱፐር ቪዥን ዘርፍ ሃላፊ አቶ አንዳርጋቸው ሞላ እንዳሉት በስልጠናው የመተከል ዞንና ወረዳ ነባርና ተተኪ አመራሮች ተሳትፈዋል።
የስልጠናው ዋነኛ አላማ በዞኑ የሚታዩ የፀጥታ ችግሮችንና አጠቃላይ የአመራር ብቃት ክፍተቶችን ለመሙላት መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው አመራሮችም ከስልጠናው የተሻለ ግንዛቤ እንደሚያገኙ ተናግረዋል።
ስልጠናው በዞኑ የሚታየውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት እንደ አንድ መፍትሄ ይታያል ያሉት አቶ አንዳርጋቸው፣ በተለይ አሁን እየመጡ ያሉ ተተኪ አመራሮች በህዝብ ይሁንታና ግምገማ የመጡ መሆናቸው ለአካባቢው መረጋጋት አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል።
አመራሩ በተለይ እውነተኛ ህብረ ብሄራዊነትና አንድነትን የሚያስቀጥልና ሁሉንም ዜጎች በእኩል ዓይን የሚያይና የአገልጋይነት መንፈስ እንዲኖረው ይረዳል ብለዋል።
በክልሉ የህግ የበላይነትን በማስከበር ላይ ያለው የፌደራል ግብረ ሃይል በመተከል ዞን ስራ ከጀመረ በኋላ አንፃራዊ ሰላም መምጣቱ ይታወቃል።