በጣና ኃይቅ ከተስፋፋው የእምቦጭ አረም ከ85 በመቶ በላዩ ተወግዷል- ኤጀንሲው

87

ባህር ዳር፣ ጥር 3/2013 (ኢዜአ) በጣና ኃይቅ ላይ ተስፋፍቶ ከነበረው የእምቦጭ አረም ከ85 በመቶ በላዩ መወገዱን የጣናና ሌሎች የውሃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ። 

በሰው ሀይልና በማሽን በመታገዝ አረሙን ማስወገድ እንደተቻለ ኤጀንሲው ገልጿል።

የኤጀንሲው የስርዓተ-ምህዳር ጥበቃና ልማት ባለሙያ አቶ ጤናው ምንውየለት ለኢዜአ እንደገለጹት የፌዴራልና የክልሉ መንግስት በመቀናጀት ህብረተሰቡንና ሌሎች አጋሮችን በማሳተፍ ባደረጉት ጥረት አረሙን ማስወገድ ተችሏል።

በደቡብና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች በሚገኙ ስድስት የጣና ኃይቅ ዙሪያ ወረዳዎች ከ4 ሺህ 300 ሄክታር በላይ የሀይቁ አካልና ዙሪያ መሬት ላይ አረሙ ተስፋፍቶ እንደነበር አስታውሰዋል።

ጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን በተካሄደ ዘመቻ ከ3ሺህ 759 ሄክታር ላይ አረሙን ማስወገድ እንደተቻለ አስታውቀዋል።

በዘመቻው በወረዳዎቹ አረሙ ከተስፋፋባቸው 30 ቀበሌዎች ውስጥ 25ቱ ሙሉ በሙሉ ነጻ መደረጋቸውን አመልክተዋል።

በጎንደር ዙሪያ ወረዳ በሶስት ቀበሌዎች አረሙን የማስወገድ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጹት ባለሙያው  በደንቢያ ወረዳ ሁለት ቀበሌዎች ባለው የውሃ ጥልቀት እስካሁን አረሙን የማሶገድ ስራ አለመጀመሩን ተናግረዋል።

በህብረተሰቡ ተሳትፎ በዘመቻው የተወገደውን አረም በተከማቸበት ቦታ አድርቆ ለማቃጠል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

"በአንድ ወቅት ዘመቻ ብቻ በሀይቁ ላይ የተከሰተን አረም በዘላቂነት ማሶገድ አይቻልም" ያሉት ባለሙያው   አረሙን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማጥፋት የተጀመረው ዘመቻ ሳይቋረጥ ለሶስት ተከታታይ አመት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመላክተዋል።  

በእምቦጭ አረም ማስወገድ ዘመቻው 397 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን የገለጹት ባለሙያው  አራት ማሽኖችም ጥቅም ላይ መዋላቸውን ተናግረዋል።

ለአረም ማስወገድ ስራው ከ61 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ መደረጉን ባለሙያው አስታውቀዋል።

"አረሙ  የእርሻ መሬት በመውረር፣ የእንስሳት ግጦሽ እንዲጠፋና  የአሳ ምርት እንዲቀንስ አድርጓል" ያሉት ደግሞ  በደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦ ከምከም ወረዳ የቅርኛ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ታከለ ሙጬ ናቸው።

"መንግስት ዘንድሮ ለችግሩ ልዩ ትኩረት በመስጠቱ ህብረተሰቡን በማስተባበር በተካሄደ ዘመቻ አብዛኛውን አረም ማሶገድ ተችሏል" ብለዋል።

በወረዳው የጤዛ አምባ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አዱኛ አስፋው በበኩላቸው "ለረጅም ጊዜ አደጋ ፈጥሮ የቆየውን የእምቦጭ አረም በዚህ ዓመት በቁርጠኝነት በተካሄደ ዘመቻ አብዛኛውን ማሶገድ ተችሏል " ብለዋል።

በዘመቻ የተወገደውን አረም ሰብሰበው ለማቃጠል የማድረቅ ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን አርሶ አደሮቹ አስታውቀዋል ።

በጣና ኃይቅ ላይ የእምቦጭ አረም ከተከሰተ ከዘጠኝ ዓመት በላይ እንደሆነው ከኤጀንሲው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም