የፌዴራል፣ የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ፖሊስ ኮሚሽነሮች የጋራ ጉባዔያቸውን እያካሄዱ ነው

63

አዲስ አበባ ጥር 3/2013 (ኢዜአ) የፌዴራል፣ የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ፓሊስ ኮሚሽነሮች 12ኛውን የጋራ ጉባዔያቸውን በቢሾፍቱ እያካሄዱ ነው።

በኮሚሽነሮቹ የጋራ ጉባዔ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የተገኙ ሲሆን የፌዴራል ፓሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤልን ጨምሮ የክልልና የከተማ አስተዳደሮች ፓሊስ ኮሚሽነሮች ታድመዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው ጉባዔ በፌዴራል ፓሊስ መዋቅራዊ አደረጃጀት እንዲሁም የማዕረግ ዕድገት አሰጣጥና ስያሜ ችግሮችና መፍትሔዎችን የሚያመላክት የጥናት ሪፓርት ይቀርባል።

ከፌዴራል ፓሊስ የደንብ ልብስ ጥራትና አቅርቦት ጋር ተያያዥነት ባላቸው ችግሮችና መፍትሔዎች እንዲሁም በኮሚሽኑ የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ውይይት እንደሚካሄድም ታውቋል።

በጉባዔው መክፈቻ ንግግር ያደረጉት ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የጉባዔው ዓላማ የአገሪቷን ፓሊስ ወደ ተሻለ ደረጃ ማሳደግ መሆኑን ገልፀዋል።

በጉባዔው ፓሊሱ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች የሚፈቱባቸውን መንገዶች የሚያመላክቱ ጥናቶች ይቀርባሉም ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እንደ አገር እንድትቀጥል መስዋዕትነት የሚከፍልላት ሠራዊት ያስፈልጋታል ብለዋል።

ይህንንም የመከላከያ ሠራዊት አባላትና የፌዴራል ፖሊሶች በተግባር ማስመስከራቸውን ገልጸዋል።

የሕግ የበላይነት እንዲከበርና እኩልነት እንዲረጋገጥ የፖሊስ ሚና የላቀ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ጉባዔው ነገም የሚቀጥል ሲሆን በክልል ፓሊስ ኮሚሽን ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ ላይ ውይይት እንደሚካሄድ ይጠበቃል።

የ6ኛውን አገራዊ ምርጫ ቅድመ ዝግጅት የሚያመለክት ዕቅድም በነገው ዕለት የሚቀርብ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም