በመተከል የዜጎች የጸጥታ ስጋት ቀንሷል፤ አንፃራዊ ሠላምም ሰፍኗል

76

መተከል ጥር 3/2013 (ኢዜአ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የተቋቋመው ግብረ ሃይል የመተከልን ዞን የጸጥታና የሕግ ማስከበር ስራ ከተረከበ በኋላ በዞኑ አንጻራዊ ሠላም ሰፍኗል፤ የዜጎች የጸጥታ ስጋትም ቀንሷል ተባለ።

የጸጥታና የሕግ ማስከበር ስራውን በአንድ ወር ጊዜ አጠናቆ ለአስተዳደሩ ለማስረከብ ዕቅድ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ያለው ግብረ ሃይሉ የሁለት ሣምንት ስራውን መገምገም ጀምሯል።

ግብረ ኃይሉ የመተከልን ዞን የጸጥታና የሕግ ማስከበር ስራ ከተረከበ በኋላ በተለያዩ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ከሕዝብ ተወካዮች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከምሁራንና ከወጣቶች ጋር ምክክር አድርጓል።

ጎን ለጎንም በሽፍታው ቡድን ላይ ሕግ የማስከበር እርምጃ በመውሰድ ተቆጣጥሯቸው የነበሩ ቦታዎችን ማስለቀቅ ተችሏል።

የአገር መከላከያ ሠራዊት በሁሉም አካባቢዎች ተሰማርቶ ሕግ የማስከበር ዘመቻ በማከናወኑ በዞኑ አንፃራዊ ሠላም ሰፍኗል፤ የዜጎች የጸጥታ ስጋትም ቀንሷል ተብሏል።

በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በተሳሳተ መረጃ ወደ ጫካ የገቡ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ እየተደረገ ስለመሆኑም ተገልጿል።

የጥፋት ቡድኑ በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸመው ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃትና የንብረት ውድመት የማንንም ብሄር የማይወክል መሆኑን ኅብረተሰቡ በተለያዩ መድረኮች ስለማረጋገጡም ተጠቁሟል።

ከጥፋት ቡድኑ ውድመት የተረፈው የአርሶ አደሮች ሰብልም ከመከላከያ ሠራዊትና ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በመቀናጀት እየተሰበሰበ ነው ተብሏል።

የጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ ኦነግ ሸኔ እና ሌሎችም የአማፂው የህወሓት ቡድን አባላት ሙሉ በሙሉ ካለተደመሰሱ በአካባቢው ዘላቂ ሠላም ለማስፈን አስቸጋሪ እንደሚሆንም ተነስቷል።

በመተከል ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የወረዳና ቀበሌ የስራ ሃላፊዎች እንዲነሱ፤ ወንጀል ያለባቸውም በሕግ እንዲጠየቁ እየተደረገ ነው።

በተጨማሪም አዲስ የሚመረጡ የስራ ኃላፊዎች ሕዝብ መምራት የሚችሉት በሕዝብ ፊት ቀርበው ተቀባይነት ሲያገኙ ብቻ በመሆኑ ይህም እየተደረገ ነው ተብሏል።

ትምህርት ቤቶችን የመማር ማስተማር ማስጀመር፣ የጤና ተቋማትን ሙሉ በሙሉ ለአገልግሎት ክፍት ማድረግና ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስ የቀጣዮቹ ሁለት ሣምንታት ስራ እንደሚሆንም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም