በአንኮበር ወረዳ ከ7 ሚሊየን ብር ባለይ ወጭ የተገነባ ሙዚየምና የባሀል ማዕከል ተመረቀ

129

ደብረ ብርሃን ጥር 02/2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በአንኮበር ወረዳ ከ7 ሚሊየን ብር ባለይ ወጭ የተገነባ የአጼ ሚኒሊክ መታሰቢያ ሙዚየምና የባሀል ማዕከል ዛሬ ተመረቀ።

የአማራ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኅላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት የሙዚየሙ መገንባት የአካበቢው ማህበረሰብ ታሪኩን ሰንዶ ለትውልድ እንዲያስተላልፍ እድል ይፈጥራል።

በአንኮበር ወረዳ የአጼ ሚኒሊክ የመናገሻ ከተማ  የበርካታ ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊና ጥንታዊ ቅርሶች መገኛ መሆኑን አመልክተዋል።

በከተማው የወጭና የሀገር ውስጥ ጎብኝዎችን ለመሳብ የሚያስችሉት ቅርሶች ዘመናዊ ማስቀመጫ ስፍራ ባለመኖር በአካባቢው ነዋሪዎች መኖሪያ ቤቶች ተቀምጠው እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

"የሙዚየምና ባህል ማዕከሉ መገንባት የተደበቁና ያልወጡ ቅርሶችን በማሰባሰብ ለእይታና ለጥበቃ በሚያመች መልኩ በማስቀመጥ ለጎብኞችና ለጥናትና ምርምር አገልግሎት ክፍት ለማድረግ ያስቸላል" ብለዋል።

የክልሉ መንግስት ወደ ሙዚየሙ የሚገቡ ቅርሶችን በአግባቡ በመጠበቅ ለጎብኞች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችል አደረጃጀት ፈጥሮ የሰው ሃይል ቅጥር እንዲፈጸም እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረጻዲቅ በበኩላቸው "የባህል ማዕከልና ሙዚየም መገንባቱ ወጣቱ ትውልድ የአባቶቹን ታሪክ በቅርበት እንዲያውቅ ያግዛል" ብለዋል።

የተገነባው ሙዝየም በህብረተሰቡ ዘንድ ተደብቀው የተቀበጡ ጥንታዊ ቅርሶችን  በማሰባሰብ ለቱሪዝም ልማት ለማዋል የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የሙዚየምና ባህል ማዕከሉ መገንባት ለአካባቢው ወጣቶች ተጨማሪ የስራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል እንደሆነም አመላክተዋል።

"በሀገራችን ካሉ ጥንታዊ ከተሞች አንዱ አንኮበር እንደመሆኑ የሙዚየሙና ባህል ማዕከሉ መገንባት ተገቢነት ያለው ነው" ያሉት ደግሞ የአንኮበር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ፈቅይበሉ ናቸው።

"ሙዚየምና የባህል ማዕከሉ ባለ አንድ ፎቅና 13 ክፍሎች ያሉት ነው " ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ህንጻው አግባብ ያለው አጥር የተገነባለትና የደህንነት ካሜራ የተገጠመለት በመሆኑ ከወዲሁ ቅርሶችን የማሰባሰብ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።

ሙዚየምና የባህል ማዕከሉን ወደ ስራ ለማስገባት የሰባት ወጣት ሰራተኞች ቋሚ ቅጥር መከናወኑን ዋና አስተዳዳሪው አስታውቀዋል።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ "ያልተለበሰ ካባ" በሚል ርዕስ በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስረቶ የተጻፈና የአካባቢውን ታሪክ፣ ባህልና ወግ የሚሳይ ልብ ወለድ መጽሃፍ ተመርቋል።።

ለሙዚየሙና ባህል ማዕከሉ ግንባታ የዋለው ገንዘብ በአካባቢው መስተዳድር፣ ተወላጆችና ህዝብ ትብብር የተሸፈነ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም