የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የድርሻችንን እንወጣለን…የምስራቅ ወለጋ ዞን ወጣቶች

112

ነቀምቴ ጥር 2/2013 (ኢዜአ) የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥና ልማትን በማስቀጠል በአገርና በመንግሥት ግንባታ ውስጥ የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን የምሥራቅ ወለጋ ዞንና የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች ተናገሩ።

በምሥራቅ ወለጋ ዞን ካሉት ወረዳዎችና ከአንድ የከተማ አስተዳደር የተውጣጡ ወጣቶች በሀገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ የወጣቱ ሚናና የዓለም ተሞክሮ በሚል ምክንያታዊ የወጣቶች መድረክ በነቀምቴ ተካሂዷል።

በመድረኩም የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ልማትን በማስቀጠል በሀገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት አብደና አመኑ በሰጠው አስተያየት ወጣቶች በአገርና በመንግሥት ግንባታ ውስጥ ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ እንደመሆኑ እሱ የሚጠበትን ኃላፊነት ለመወጣት ተዘጋጅቷል።

እሱን ጨምሮ ወጣቶች ያለፈውን ታሪክ በማስታወስ፣ የአሁኑን በመገንዘብና የወደ ፊቱን በማሰብ የበለጸገች፣ ሠላሟ የተረጋገጠና ለዜጎቿ የተመቸች አገር ለመጪው ትውልድ በማስተላለፍ ታሪክ የመስራት ግዴታ እንዳለባቸው መገንዘቡንም አስረድተዋል።

የሰላም ዋጋ የማይተመን መሆኑን የተናገረው ወጣት አብደና ከወጣቱ የአከባቢውን የሕግ የበላይነት በማረጋገጥ ልማትን በማስቀጠልና በአገሪቱ እውነተኛ ፌዴራሊዝም እውን እንዲሆን የበኩሉን አስተዋጽኦ መወጣት እንደሚጠበቅም ገልጿል።

የነቀምቴ ከተማ ነዋሪ ወጣት ብርሃኑ ኤቢሣ በበኩሉ የዞኑና የከተማው ወጣቶች ሀገራቸውን የሚወዱና በአገር ግንባታ ውስጥ የድርሻቸውን እየተወጡ የሚገኙ መሆናቸውን ተናግሯል።

ለወደፊቱም በሀገሪቱ የመንግሥትና የአገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የሚጠበቅባቸውን ትልቅ ኃላፊነት በመወጣት ለልማቱ አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል።

የቦነያ ቦሼ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ደረሰ ተስፋዬም ወጣቶች የለውጥ ኃይል በመሆናቸው በአገሪቱ ልማት፣ ሠላምና ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ ከመንግሥት ጎን በመሆን የድርሻውን ለመወጣት መዘጋጀቱን አመልክቷል።

የምሥራቅ ወለጋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ደረጀ አበራ በበኩላቸው ወጣቱ ግንባሩን ለጥይት በመስጠት የመጣውን ለውጥ ለመጠበቅም ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበትም አሳስበዋል።

ወጣቱ በመንግሥትና ሀገር ግንባታ ውስጥ የድርሻውን ከተወጣ ታሪክ ለዘላለም እንደሚያስታውሰው ገልጸው የዞኑንና የከተማውን ሠላም በመጠበቅ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በትጋት መስራት እንዳለበትም አስታውቀዋል።

የነቀምቴ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ባህሩ ኤባም ወጣቱ በአገር ግንባታ ውስጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት አሳስበው ሚዛናዊ አስተሳሰብን በማዳበር ሲደግፉም ሆነ ሲቃወሙ ምክንያታዊ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

በነቀምቴ ከተማ ትላንት በተካሔደው የውይይት መድረክ ከዞኑና ከነቀምቴ ከተማ የተወጣጡ ከ 500 የሚበልጡ ወጣቶች እንዲሁም አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም