በበጀት ዓመቱ 5 ወራት ዳያስፖራው 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ወደ ኢትዮጵያ ልኳል - የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ

73

አዲስ አበባ ጥር 2/2013 (ኢዜአ) በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ አምስት ወራት ዳያስፖራው 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር /ሬሚታንስ/ ወደ ኢትዮጵያ መላኩን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ደግሞ 35 ዳያስፖራዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ መግባታቸው ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ዳያስፖራው ሕጋዊ መንገዶችን እንዲጠቀም በተከናወኑ ስራዎች በ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪ አምስት ወራት 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር መላኩን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ይህ ኤጀንሲው በበጀት ዓመቱ ዳያስፖራው 4 ቢሊዮን ዶላር እንዲልክ ካስቀመጠው እቅድ አንጻር ብዙ መስራት እንደሚጠበቅበት የሚያመላክት ነው ብለዋል።

ገንዘቡ ከሰሜን አሜሪካ፣ ከአውሮፓ፣ ከመካከለኛ ምስራቅ፣ ከእስያና ከአፍሪካ መላኩንና በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሚልኩት የገንዘብ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን አክለዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ያስከተለው ጉዳት አንዱ ፈተና እንደሆነና በተለያዩ ዘርፎች የሚሰሩ ዳያስፖራዎች ላይ ወረርሽኙ ተጽዕኖ ማሳደሩንም አመልክተዋል።

ይሁንና ወረርሽኙ በሬሚታንስ አፈጻጸሙ ላይ የተፈራውን ያህል ተጽዕኖ አለማሳደሩን ገልጸዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የክትባት ስርጭት ሲስፋፋ የተሻለ የስራ እንቅስቃሴ እንደሚኖር ተስፋ እንደሚደረግና በዚህም በዓመቱ የታሰበውን ዕቅድ ለማሳካት የተሻለ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ዳያስፖራው ገንዘቡን ሕጋዊውን መንገድ ብቻ ተጠቅሞ ወደ አገር ቤት እንዲልክ የሚያስችሉ ተግባራት ላይ ኤጀንሲው ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

ዳያስፖራውም ሕጋዊ መንገድ ተጠቅሞ ገንዘቡን ወደ አገሩ ቢልክ ራሱንም አገሩንም ተጠቃሚ ማድረግ ይችላል ብለዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በ2013 በጀት ዓመት ስድስት ወራት 2 ሺህ 637 ዳያስፖራዎች የባንክ ሂሳብ ቁጥሮችን በመክፈት 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ተቀማጭ ማድረጋቸውን ነው ወይዘሮ ሰላማዊት የገለጹት።

በተመሳሳይ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት 35 ዳያስፖራዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቅሰዋል።

አማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች እንዲሁም አዲስ አበባ ዳያስፖራዎቹ ወደ ስራ የገቡባቸው ቦታዎች ሲሆኑ ግብርና፣ ሆቴልና ቱሪዝምን ጨምሮ ሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች ላይ መሰማራታቸውን ገልጸዋል።

በቀሪው የበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ቀደም ብለው ጥያቄ ያቀረቡት 847 ኢንቨስተሮች በተቀመጡ መስፈርቶች ከተለዩ በኋላ ወደ ስራ እንዲገቡ ይደረጋልም ብለዋል።

ዳያስፖራው ከአገልግሎት ዘርፉ በተጨማሪ በአምራች ዘርፍ ላይ ቢሳተፍ አዋጭ እንደሚሆንና ለዚህም ኤጀንሲው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ወይዘሮ ሰላማዊት ተናግረዋል።

በስድስት ወራት ውስጥ ከኢንቨስትመንት በተጨማሪ 928 ዳያስፖራዎች በተለያዩ የንግድ መስኮች ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ መግባታቸውንም አክለዋል።

በተጨማሪም በዳያስፖራዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ አሰጣጥና ወደ ስራ ለመሰማራት የሚታዩ የአሰራር ችግሮችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን መፍትሔ የመስጠት ስራ እንደሚከናወን አስተውቀዋል።

 በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት ዳያስፖራው 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ወደ አገር ቤት መላኩን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

በተጨማሪም በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት 33 ዳያስፖራዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ መግባታቸውንም ኤጀንሲው ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም