ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ የመጨረሻ ከፍተኛ ወታደራዊ ኒሻን ተሸለሙ

115

ጥር 2/2013 (ኢዜአ) የኢፌዴሪ መከላከያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ፣ ከጂቡቲ መከላከያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ዘከሪያ ሼህ ኢብራሂም የአገሪቱ የመጨረሻ ከፍተኛ ወታደራዊ ኒሻን ተበረከተላቸው።

በኒሻን ማልበስ ስነስርዓቱ የተገኙት የሰላም ማስከበር ማዕከል ኃላፊ ሌተናል ጀነራል ደስታ አብቼ ለኢትዮዽያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት፣ ጀነራል ብርሃኑ ከጂቡቲ መንግስት የተበረከተላቸው ኒሻን በአገሪቱ ፕሬዚዳንት ተፈቅዶ የተሰጣቸውና የመጨረሻ ከፍተኛ ደረጃ ኒሻን ነው።

ጀነራል ብርሃኑ በወታደራዊ የአመራር ክህሎታቸው ባሳዩት ድንቅ የመሪነት ብቃት በአገራችን አጋጥሞ የነበረው አደጋ እንዲቀለበስ በማድረግና ህግ የማስከበሩን ተግባር የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በአኩሪ ጀግንነት እንዲፈፅም የመሪነት ሚናቸውን በመወጣት ኢትዮዽያና የአካባቢው አገራት ከተጋረጠባቸው ከፍተኛ አደጋ በማዳናቸው መሆኑንም ገልፀዋል።

በኒሻን ማልበስ ስነስርዓቱም የጂቡቲ መከላከያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ዘከሪያ ሼህ ኢብራሂም፣ የጀነራል ብርሃኑ ጁላን የመሪነት ብቃት አድንቀው፣ ጉዳቱን መከላከል ባይቻል ኖሮ ኢትዮዽያን በመበተን ብቻ ሳይቆም የአካባቢው አገራትን የሚበትን አደገኛ ሁኔታ ያጋጥም ነበር ማለታቸውን ጠቁመዋል።

ከአደጋው ሁላችንም እንድንድን ባደረጉት የኢትዮዽያ መከላከያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ጠንካራ አመራር ኮርተናል በማለትም ሽልማቱን ማበርከታቸውን የሰላም ማስከበር ኃላፊው ገልፀዋል።

ጀነራል ዘከሪያ ሼህ ኢብራሂም ጂቡቲና ኢትዮዽያ ያላቸው ታሪካዊ ወዳጅነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በስነስርዓቱ አረጋግጠዋል።

ሽልማቱ የተበረከተላቸው የኢፌዴሪ መከላከያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ፣ የአገሪቱን ከፍተኛ የመጨረሻ ኒሻን ላበረከተላቸው የጂቡቲ ህዝብና መንግስት በኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊትና በኢትዮዽያ ህዝብ ስም ምስጋና ማቅረባቸውን የሰላም ማስከበር ኃላፊው ሌተናል ጀነራል ደስታ ገልፀዋል።

በሽልማቱ ታላቅ ኩራትና ክብር እንደተሰማቸው ጠቁመው፣ የሁለቱ አገሮች የህዝብ ለህዝብ ታሪካዊ ግንኙነትና አገራዊ ወዳጅነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለፃቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።

በስነስርዓቱ አገራቱን የሚወክሉ የተለያዩ የድል መዝሙሮች መቅረባቸውንና የአገራቱ የሁለትዮሽ ውይይት መደረጉንም ኃላፊው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም