በማእከላዊ ጎንደር ዞን የሩዝ አመራረትን ለማዘመን እየተሰራ ነው- የዞኑ ግብርና መምሪያ

1927

ባህር ዳር፣  ጥር 1/2013(ኢዜአ) በማእከላዊ ጎንደር ዞን በ2012/13 ምርት ዘመን በሩዝ ሰብል ከተሸፈነው የእርሻ መሬት ከሩብ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ዮሃንስ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደተናገሩት በምርት ዘመኑ በዞኑ ሩዝ አብቃይ በሆኑ 8 ወረዳዎች 6ሺህ 678 ሄክታር መሬት በሩዝ ማልማት ተችሏል።

በምርት ዘመኑ በዞኑ በምእራብና በምስራቅ ደንቢያ በጎንደር ዙሪያ በጭልጋና በጣቁሳ ወረዳዎች የሚገኙ አርሶአደሮች ከፍተኛ ሩዝ ማምረት እንደቻሉም ተናግረዋል።

መምሪያው ለሩዝ አምራች አርሶ አደሮች በሽታን፣ ተባይንና የዝናብ እጥረትን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት መስጠት የሚችሉ የሩዝ ዝርያዎችን በማቅረብ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል። 

በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የሸሃ ጎመንጌ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሙላት አስማረ በ2012/13 ምርት ዘመን በሩዝ ካለሙት አንድ ሄክታር መሬት 40 ኩንታል የሩዝ ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

የሩዝ ሰብልን ፍሬውን ከገለባ ለመለየት የሚጠቀሙት በእህል ወፍጮና በሙቀጫ በመሆኑ የምርት ጥራት መጓደል እያጋጠማቸው መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስት የሩዝ አምራች አርሶ አደሮችን ችግር ተገንዝቦ ዘመናዊ የሩዝ መፈልፈያ ማሽን እንዲያቀርብላቸውም ጠይቀዋል። 

በምእራብ ደንቢያ ወረዳ የሮቢት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር በለጠ አሸናፊ በባህላዊ መንገድ የሚያመርቱት ሩዝ ገበያ ላይ በዘመናዊ መንገድ ከሚመረተው ሩዝ በኪሎ 10 ብር ቅናሽ በማድረግ ለመሸጥ መገደዳቸውን ተናግረዋል።

የሩዝ ሰብልን ፍሬውን ከገለባ ለመለየት የሚጠቀሙት በባህላዊ ሙቀጫና ወፍጮ በመሆኑ የምርት ጥራት መጓደልና ምርቱም በገበያ ተወዳዳሪ ሊያደርጋቸው ባለመቻሉ መንግስት ዘመናዊ የሩዝ መፈልፈያ ማሽን እንዲያሟላ አሳስበዋል።

በምርት ዘመኑም በሩዝ ካለሙት ግማሽ ሄክታር 19 ኩንታል የሩዝ ምርት ማግኘት እንደቻሉም አስረድተዋል።

በዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ዮሐንስ ተስፋዬ እንደገለጹት በዚህ አመት በምእራብና ምስራቅ ደንቢያ እንዲሁም ጎንደር ዙሪያ ወረዳ ለሚገኙ ሩዝ አምራች አርሶ አደሮች አምስት ዘመናዊ የሩዝ መፈልፈያ ማሽኖችን ለማቅረብ እየተሰራ ነው።

ለዚሁ ስራ ተብሎ የተገዙት ማሽኖችም ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን ጠቁመው፤ በሰአት 70 ኩንታል ሩዝ የመፈልፈል አቅም ያላቸው መሆናቸውንም አስረድተዋል።

በወረዳዎቹ ለተደራጁ የዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ወጣቶች ማሽኖቹን በረዥም ጊዜ ክፍያ በማስረከብ የአርሶ አደሮቹን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።