የብር ለውጡን ተከትሎ ገንዘብ በፋይናንስ ስርዓት እንዲያልፍ በመደረጉ ወንጀል እየቀነሰ ነው- የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል

132

አዲስ አበባ፣ ጥር 1 /2013 ( ኢዜአ) የብር ለውጡን ተከትሎ ማንኛውም ገንዘብ በፋይናንስ ስርዓት እንዲያልፍ በመደረጉ ወንጀል እየቀነሰ መሆኑን የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል አስታወቀ።

አዲሱን የብር ኖት አስመስለው በማተም ወንጀል የውጭ ዜጎችም ጭምር መሳተፋቸው ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ከመስከረም 4 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የ10፣ የ50 እና የ100 ብር ኖቶቿን በአዲስ ስትቀይር ከዚህ በፊት ያልነበረ የ200 ብር ኖት ጥቅም ላይ አውላለች።

በማዕከሉ የክትትልና ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ ሙሉጌታ ተመስገን ለኢዜአ እንዳሉት የብር ኖት ቅያሬው ለህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች የሚደረግ ድጋፍን ጨምሮ ሙስናንና የኮንትሮባንድ ሥራዎችን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ሚና አለው።

የብር ለውጡን ተከትሎ ማንኛውም ገንዘብ በፋይናንስ ስርዓት እንዲያልፍ በመደረጉ ወንጀል እየቀነሰ መሆኑንም ገልፀዋል።

በግለሰቦች እጅ ያለ ገንዘብ የታክስ ስርዓቱን ለማበላሸትና ወንጀልን በቀላሉ ለመስራት አጋዥ መሆኑን የገለጹት አቶ ሙሉጌታ የብር ኖት ቅያሬው ውጤታማ እንዳይሆን የጣሩ መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በዚህም ከውጭ የተደራጁ ኃይሎች ተቀናጅተው አዲሶቹን የብር ኖቶች አስመስሎ በማተም ለማሰራጨት ሙከራ አድርገው በጠንካራ ክትትል መክሸፉን ገልጸዋል።

ከአፍሪካ አገራት አንዳንድ ግለሰቦች በአገር ወስጥ ካሉ ወንጀለኞች ጋር በመደራደር በህገ-ወጥ ድርጊቱ ላይ ተሳታፊ እንደነበሩ ጠቅሰዋል።

በዚህ ጉዳይ የኢሚግሬሽንና ዜግነት ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ከውጭ የሚገቡ ሰዎችን ማንነት በመለየት በኩል ጠንካራ ክትትል ማድረግ ይኖርበታል ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በሌላ በኩል የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው ሀሰተኛ የብር ኖቶች እንዲሰራጩ በማድረግ ቅያሬውን ለማደናቀፍ ሙከራዎች ማድረጋቸውን አንስተዋል።

የብር ኖት ቅያሬውን ተከትሎ በግለሰቦች ዘንድ በቀን ከ200 ሺህ ብር በላይ፣ በኩባንያዎች ደግሞ ከ300 ሺህ ብር በላይ ከባንክ በጥሬ ገንዘብ እንዳይወጣ ብሔራዊ ባንክ መመርያ ማውጣቱ ይታወቃል።

በዚህ መመሪያ መሰረት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ከባንክ ውጪ ይዞ መገኘት ተጠያቂ እንደሚያደርግና የተከለከለ መሆኑም እንዲሁ።

በኢትዮጵያ አዲስ የብር ኖት ቅያሬ የተደረገው ከ23 ዓመታት በኋላ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም