ኢትዮጵያውያንን ያስተሳሰረ ሌላኛው የወል ፕሮጀክት

73

በጥላሁን አያሌው (ኢዜአ)

ኢትዮጵያውያን ለጋራ ጉዳያቸውና ሀገራቸውን በሚመለከት ማናቸውም ሁነት ትናንትም ይሁን ዛሬ የማይናወጥ ጠንካራ አቋም አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ በተለያዩ ወቅቶች የገጠሟትን ፈታኝ ምዕራፎች የተሻገረችው ህዝቦቿ ባላቸው የመተባበር ባህል ነው። ኢትዮጵያውያን ባላቸው ጥልቅ ሀገራዊ ፍቅርና ለሉአላዊነት በከፈሉት መስዋዕትነት ሀገሪቱ ታፍራና ተከብራ ኖራለች፤ ይህም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ላይበጠስ የተገመደ ላይላላ የተቋጠረ ጠንካራ ሀገራዊ አንድነት እንዲኖራቸው አድርጓቸዋል።

የኢትዮጵያውያን አንድነትና ህብረት ለመላው ዓለም ማስረጃ ከሆኑ ዐበይት ሁነቶች መካከል ዘመን አይሽሬውና ዓለም እንደ እንቆቅልሽ የሚያወሳው ታላቁ የአድዋ ድል ነው። የአድዋ ጦርነት እስከዛሬ ድረስ ለዓለም እንቆቅልሽ የሆነው በአብዛኛው ባህላዊ መሳሪያ የታጠቀው የኢትዮጵያ ሠራዊት ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀውን የጣሊያን ሠራዊት ድባቅ መምታት መቻሉ ነው። ሬይመንድ ጆናስ የተባለው የታሪክ ምሁርThe Battle of Adwa: African Victory in the Age of Empire” በሚል ርዕስ በጻፈው መጽሐፉ ላይ የአድዋ ድል የዓለምን የታሪክ አቅጣጫ የወሰነ ድል ነው ሲል ጽፈዋል። ጸሐፊው እንደጠቀሱት የአድዋ ድል ለኢትዮጵያ የቅኝ አገዛዝን እንድትቀለብስ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ሉአላዊነቷን እንድታስከብር አድርጓታል በማለት ገልጾታል። 

ይህ ዓለምን የስደመመው የአድዋ ድል በተናጥል የተገኘ ድል አይደለም። ኢትዮጵያውያን ከጫፍ እስከ ጫፍ በአንድነት ዘምተው በተባበረ ክንድ ለሀገራቸው ክብርና ሉዓላዊነት የተዋደቁበት ብሔራዊ ገድል እንጂ። በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን የአብሮነት ደማቅ ታሪካቸውን የከተቡበት ታላቅ ትርጉም ያለው እለት ነው።

በዚህ ዘመንም ኢትዮጵያውያን አብሮነታቸውን ያሳዩባቸው በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ የታየው አንድነት ብዙዎች ከአድዋ ድል ጋር ያመሳስሉታል። መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም መሠረቱ የተጣለው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በሚያዋጣው መዋጮ እየተገነባ የሚገኝ ሲሆን ለሀገራችን ዕድገትና ብልጽግና ካለው ወሳኝ ሚና ባሻገር ሀገሪቱን ከፍ እንድትል የሚያደርግም ነው።

የህዳሴው ግድብ ግንባታ ሲጀመር ኢትዮጵያ ለፕሮጀክቱ ብድርም ይሁን እርዳታ እንዳታገኝ ከፍተኛ ተጽእኖ ሲደረግ ነበር። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያን እጃቸውን አጣጥፈው ከመቀመጥ ይልቅ የግድቡን ግንባታ በቆራጥነት ጀምረው አሁን ላይ 78 በመቶ አድርሰውታል። ይህንን በማድረግም በራሳቸው አቅም ይህን መሰል ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መገንባት እንደሚችሉ አስመስክረዋል። የህዳሴው ግድብ ኢትዮጵያውያን ዛሬም ለጋራ ጉዳያቸው በጋራ መቆም እንደሚችሉ ያሳዩበት ተምሳሌትም ሆኗል። ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ አስተዋጽኦ እያደረገ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ አሁንም አብሮነቱን ከፍ አድርጎ የሚያሳይበት ሌላ ፕሮጀክት ጀምሯል፤ገበታ ለሀገር።

የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ኢትዮጵያውያን በአድዋ ድል እና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሳዩትን የአብሮነት ዘመቻ በገበታ ለሀገር ለመድገም ተነስቷል። ይህም ኢትዮጵያውያን ትናንትም፣ ዛሬም ሆነ ወደፊት በጋራ ጉዳዮች ላይ የማይናወጥ ጽኑ አቋም እንዳላቸው ማረጋገጫ ነው። የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በአማራ ጎርጎራን፣ በኦሮሚያ የወንጪ ሀይቅን እና በደቡብ ኮይሻን ለማልማት የሚከናወኑ ሦስት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን የያዘ ሲሆን ዓላማውም በህዝብ መዋጮ፣ በትብብርና በአብሮነት ለሀገሪቱ እድገትና ብልጽግና መሠረት መጣል ነው። ለሦስቱ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ቢያንስ ስድስት ቢሊዮን ብር ያህል እንደሚያስፈልግ መረጃዎች ያሳያሉ።

ይህን ፕሮጀክት እውን ለማድረግ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ተቋማት እና መላ የሀገራችን ዜጎች የገንዘብ አስተዋጽኦ ማድረግ ጀምረዋል። በርካታ የመንግሥትና የግል ተቋማት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ገቢ እያደረጉ ሲሆን ኢትዮጵያውያን በክልል ሳይገደቡ እርስ በርስ በመደጋገፍ መንፈስ ተሳትፏቸውን ቀጥለዋል። 

ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ “ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት” በሚል ስያሜ የተጀመሩና ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑት በታላቁ ቤተመንግስት ውስጥ የአንድነት ፓርክን ጨምሮ የሸገር ፓርክ እንዲሁም የእንጦጦ ፓርክ ግንባታዎች በህዝቡና በተለያዩ ድርጅቶች ድጋፍ የተገነቡ ሲሆን ይህም የአብሮነት እሴቶቻችን ዳግም እንዲጎሉ አድርጓል። ሸገርን በማስዋብ ከተገኘው ልምድ በመውሰድ የተጀመረው ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በአጭር ጊዜ እንደሚጠናቀቅም ይጠበቃል።

ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በግንባታ ሂደት ላይም ሆነ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ሲሆን ለበርካቶች የሥራ እድል ከመፍጠራቸውም በተጨማሪ የሀገርን ገፅታ በመቀየር ለሀገር ውስጥና ለውጭ ጎብኚዎች መስህብ በመሆን ያገለግላሉ። ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ቱሪዝምን ከማስፋፋትና ገጽታን ከመገንባት ባሻገር ለነዋሪዎች ምቹ አካባቢን ከመፍጠር አኳያ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ የፕሮጀክቱን መጀመር ይፋ ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት በሀገሪቱ ያሉ እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶችን በቀላሉ መሠረተ ልማት በመዘርጋትና በማልማት ለዜጎችም ይሁን ለውጭ ጎብኚዎች ምቹ የመዝናኛ ማዕከል ማድረግ ይቻላል።

ኢትዮጵያ የዓለምን ቀልብ የሚስቡ በርካታ ተመራጭና ተወዳጅ የቱሪዝም መስህቦች ያሏት፣ የድንቃ ድንቅ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ መስህቦች ባለቤት ናት። ረዥም ዕድሜ ያስቆጠሩ ቤተ እምነቶች፣ የታሪክና የሥልጣኔ መገለጫ የሆኑ ኪነ ህንጻዎች፣ የብዝሀነቷ ማሳያዎች፣ ባህላዊ ትውፊቶች እንዲሁም ብርቅዬ እንስሳትና ልዩ ልዩ ዝርያ ያላቸው ዕጽዋት ይገኙባታል። በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የተለያዩ የመስህብ ቦታዎች ቢኖሩም ትኩረት ባለማግኘታቸው ጥቅም ላይ ሳይውሉ ቆይተዋል።

በእነዚህ ፕሮጀክት የታቀፉ የመስህብ ሥፍራዎች አስታዋሽ በማጣት ለዘመናት ያለምንም አገልግሎት ባክነው የቆዩ በመሆናቸው አሁን አካባቢዎቹን ለማልማት የተጀመረው ሥራ በአካባቢዎቹ ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ደስታን ፈጥሯል። ይህ ሀገራዊ ፕሮጀክት በሌሎች ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በቀጣይ እየተስፋፋ የሚሄድ ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያውያንን በአንድነት ያጋመደ ሰንሰለት ነው። እናም ኢትዮጵያውያን ዛሬም እንደወትሮው ሁሉ ለአንድ ዓላማ በጋራ በመዝመት በራሳችን አቅም ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ሰርተን ማጠናቀቅን እንደምንችል ለዓለም ማሳየታችንን እንቀጥላለን!!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም