ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትን ጎብኙ

66
አዲስ አበባ ሐምሌ 15/2010 የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራርና አባላት ዛሬ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መስሪያ ቤትን የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኙ። የፓርቲ አመራሮቹ ተቋሙን የጎበኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት ነው ተብሏል። የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል አደም መሃመድ ተቋሙ ከምስረታው አንስቶ እስካሁን ድረስ ያለፋቸውን ሁኔታዎች አስመልክተው ገለጻ አድርገዋል። ጄነራል አደም በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ ተቋሙ በርካታ አዎንታዊ አስተዋጽዖዎችን ያከናወነ ቢሆንም መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮች መኖራቸውንም ጠቁመዋል። ከኃይለ ሥላሴ የሥልጣን ዘመን አንስቶ ኢህአዴግ ስልጣን እስከያዘበት ጊዜ ድረስ ተቋሙ ከፖለቲካ ነጻና ገለልተኛ ስለመሆኑ በህግ  ካለመደንገጉም በላይ ክፍተቶችም ታይቶበታል ብለዋል። በሕግ ከተሰጠው ሥልጣን ውጪ በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው የሚያዙ ሰዎችን ደብቆ የመያዝ እንዲሁም የመመርመር ሥራ ውስጥ መግባቱን ጄነራሉ በአሉታዊ ጎኑ አንስተዋል። ስትራቴጂካዊ ፋይዳ ያላቸው የኢንተሊጄንስ ጥናቶችና ትንበያዎች በማዘጋጀትና ለመንግሥት በማቅረብ በኩልም ተቋሙ ክፍተት የነበረበት መሆኑን አስረድተዋል። ተቋሙ እነዚህንና ሌሎች ክፍተቶችን ለመሙላት የማሻሻያ ሥራ እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት ጄነራል አደም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ተቋሙን አንዲጎበኙ የተደረገውም ሀሳባቸውን ለማካተት በማሰብ ጭምር መሆኑን ገልፀዋል። የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ በሰጡት አስተያየት በዛሬው እለት ተቋሙን መጎብኘታቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ኃሳብ ወደ መሬት እየወረዱ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ነው ብለዋል። የተቋሙ ቅጥር ግቢ ለፓርቲዎቹ ክፍት መሆኑ በራሱ ደስታ እንደጫረባቸው ተናግረዋል። ተቋሙን በአሉታዊ መልኩ ሲመለከቱት እንደነበረ ያወሱት ጎብኚዎቹ ተቋሙ ያቀደውን የማሻሻያ ሥራ በተመለከተ የተደረገላቸው ገለፃም አዎንታዊ አተያይ እንደፈጠረባቸው ገልፀዋል። የአንድነት ፓርቲ ሊቀ-መንበር አቶ ትዕግስቱ አወሉም ይህ ጉብኝት እንዳስደሰታቸውና በእርግጥም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የለውጥ ሥራ እየታየ መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል። ተቋሙ ከዚህ ቀደም የማይታወቅ እንደነበርና ዛሬ ግን ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ጭምር ክፍት መደረጉ ለውጡን የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል። ከዚህ ቀደም ለተቋሙ የነበራቸው አመለካከት በእጅጉ አሉታዊ እንደነበር የተናገሩት የቅንጅት ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ አየለ ጫሚሶ በበኩላቸው በተቋሙ ቅጥር ግቢ ውስጥ በመገኘት ጉብኝት ማድረጋቸው ያላቸውን አመለካከት እንደቀየረላቸውና ከታሰበው ለውጥ ጎን እንደሚቆሙ  አረጋግጠዋል። የራዕይ ፓርቲ ፕሬዝዳንት ተሻለ ሰብሮ በሰጡት አስተያየት ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ይህንን ተቋም መጎብኘታቸው "ጥቁር መጋረጃ የተቀደደ ያህል ነው"  በማለት ክስተቱን ገልፀውታል። ለዚህ አባባላቸው የጠቀሱት ምክንያት ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚባል ደረጃ የፖለቲካ ፓርቲዎች የደህንነት መሥሪያ ቤቱን የበላይ አመራሮች መተዋወቅ መቻላቸውን ነው። ለዚህ ትልቅ ለውጥ መሳካት ፓርቲያቸውም ከተቋሙ ጎን ይቆማል ብለዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ዛሬ ማለዳ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም