በክልሉ የህዳሴ ግድቡን ከደለል ለመጠበቅ የሚያግዙ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች እንደሚካሄድ ተገለጸ

91

አሶሳ፣ ታህሳስ 30 / 2013(ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተያዘው የበጋ ወቅት የህዳሴ ግድቡን ከደለል ለመጠበቅ የሚያግዙ ከአንድ ሺህ 300 በላይ ንኡስ ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡

በክልሉ ለሁለት ወራት በዘመቻ  የሚካሄድ የበጋ ወቅት አፈርና ውሃ ጥበቃ ዘመቻ በባምባሲ ወረዳ መንደር 45  ዛሬ በይፋ ተጀምሯል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ባበክር ከሊፋ ዘመቻውን ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት፤ የተፋሰስ ልማት ሥራው በክልሉ በዓባይ ተፋሰስ ላይ ያተኩራል፡፡

ከአንድ ሺህ 300 በላይ ንኡስ ተፋሰሶችን የሚሸፍነው ይኸው ዘመቻ የህዳሴ ግድብን ከደለል ለመጠበቅ ያለመ ነው ብለዋል፡፡

ዘመቻው ለሁለት ወራት የሚዘልቅ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ባበክር ፤የአካባቢ ጥበቃ ሥራው በተፋሰሱ ውስጥ የሚገኙ ከ32 ሺህ 366 ሄክታር መሬት እንደሚሸፍን አስረድተዋል፡፡

ከ160 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እና ሌሎች የክልሉ ነዋሪዎች እንደሚሳተፉ  ይጠበቃል፡፡

ይህንኑ የልማት ሥራ  ውጤታም ለማድረግ የክልሉ መንግስት ከ10 ሺህ በላይ አካፋ፣ ዶማ እና ሌሎችንም ቁሳቁሶች ማሰራጨቱን አስታውቀዋል፡፡

የባምባሲ ወረዳ ዋና አስዳዳሪ አቶ አብዱላሂ መሃመድ በበኩላቸው፤  በበጋው ወራት የሚከናወነው  የተፋሰስ ልማት አካባቢውን ከመራቆት በመጠበቅ ረገድ ውጤት ማምጣቱን ተናግረዋል፡፡

በወረዳው የጠፉ ምንጮች እና የተራቆቱት ደኖች መመለስ በመጀመራቸው የአየር ንብረት ለውጥ እና የእርሻ መሬት ለምነት እንዲመለስ ማስቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

የጠፋውን የተፈጥሮ ሃብት መልሶ መተካት መትጋት እንደሚጠይቅ የገለጹት ደግሞ በልማት ዘመቻው እየተሳተፉ ካሉት የአካባቢው አርሶ አደሮች መካከል ወይዘሮ ስንታየሁ ካሚል ናቸው፡፡

የተፋሰስ ልማትን ጥቅም ከተረዱ የአካባቢው ነዋሪዎች ጋር  በዘመቻው  በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይህም የለማ መሬት ለትውልድ ለማስተላለፍ ወሳኝ እንደሆነ  ወይዘሮ ስንታየሁ ገልጸዋል፡፡

ሌላው አርሶ አደር እንድሪስ አህመድ በበኩላቸው፤ አካባቢው ከ30 ዓመት በፊት ጥብቅ የቀርከሃ ደን እንደነበርና  አግባብነት በጎደለው አጠቃቀም የተፈጥሮ ሃብቱ መውደሙን አስታውሰዋል፡፡

ተፋሰስን መሰረት ባደረገው  የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ከተጀመረ በኋላ አካባቢው ማገገሙን የተናገሩት አርሶ አደር እንድሪስ፤ በዚህም የመኖር ተስፋችንን አለምልሟል ብለዋል፡፡

በጋራ የተፋሰስ ልማት ያገኙትን ውጤት በግል ማሳቸው ለማስፋፋት ማቀዳቸውንም ገልጸዋል፡፡

በአሶሳ ዞን ባምባሲ ወረዳ  ዛሬ በተጀመረው የተፋሰስ ልማት ሥራ ላይ አርሶ አደሮች እና ሌሎች በየደረጃው የሚገኙ  አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም