ኮሌጁ ያደረገላቸው ድጋፍ የመማር ማስተማሩ ሥራ ለማሳካት እንደሚያግዛቸው መምህራንና ተማሪዎች ገለጹ

68

ጎባ፣ ታህሳስ 30/2013(ኢዜአ)  በሮቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የተደረገላቸው የማጣቀሻ መጽሃፍትና የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ድጋፍ የመማር ማስተማሩ ሥራ ለማሳካት እንደሚያግዛቸው ድጋፉን ያገኙ ትምህርት ቤቶች መምህራንና ተማሪዎች ገለጹ።

ኮሌጁ  አጋርፋና ሲናና ወረዳዎች ለሚገኙ ሁለት ትምህርት ቤቶች 400 የማጣቀሻ መጽሃፍትና ሌሎች የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ድጋፍ ማድረጉን አመልክቷል፡፡

ድጋፍን ካገኙት  መካከል የአሊ ከጀዋ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ስሜ አሰፋ እንዳሉት በኮሌጁ 200  የማጣቀሻ መጽሃፍት፣ የቤተ ሙከራ መስሪያ የቤት ክዳን ቆርቆሮና ጥቁር ሰሌዳ ሰጥቷቸዋል፡፡

ይህም ለመማርና ለማስተማር ለማሳካት የሚደረገውን ጥራት በመደገፍ እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።

የአሎሴ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ጉታ ማሞ በበኩላቸው ኮሌጁ ያደረገው ድጋፍ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

ኮሌጁ  ያደረገላቸው ድጋፍ በትምህርት ቤታቸው ያለውን የኮምፒተርና ማጣቀሻ  መጽሃፍት እጥረት ለማቃለል እንደሚረዳቸው  የገለጸችው ደግሞ የአሊ ከጀዋ ትምህርት ቤት የስድስተኛ  ክፍል ተማሪ ሀስና ከሊል ናት፡፡

ሌላዋ  የትምህርት ቤቱ ተማሪ ሀስና አሎ በሰጠችው አስተያየት  በተለይ  የኮምፒተሩ  ድጋፍ ከቴክኖሎጂ ጋር በቅርበት እንድንተዋወቅ እድል ይፈጠርልናል ስትል ገልጻለች፡፡ 

የኮሌጁ ዲን አቶ ከድር ገቢ እንደገለጹት ከመማር ማስተማር ስራ በተጓዳኝ በአቅራቢያው በሚገኙ የተመረጡ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚታዩ የመማሪያ ቁሳቁስ አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት እየሰሩ ነው፡፡

ለሁለት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያደረግነው የማጣቀሻ መጽሃፍትና ሌሎች የትምህርት መርጃ ቁሳቁሶች የዚሁ ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡

በተለይ ለትምህርት ቤቶቹ የተደረገው የማጣቀሻ መጽሃፍት ድጋፍ የተማሪዎችን የንባብ ባህል በማዳበር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

ለትምህርት ቤቶቹ የተደረገው ድጋፍ 400 የማጣቀሻ መጽሃፍት፣ ጥቁር ሰሌዳና ኮምፒተር እንዲሁም 100 የቤት ክዳን  ቆርቆሮ  መሆኑን አመልክተዋል።

የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ናሲር አህመድ  ኮሌጁ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች እጥረት በሚታይባቸው ትምህርት ቤቶች ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የሮቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ተቋርጦ የነበረውን ትምህርት በጤና ሚኒስቴር ፕሮቶኮል መሰረት በማስቀጠል እጩ መምህራንን እያስተማረ እንደሚገኝ ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም