በወላይታ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የሚያግዝ የሀገር ሽማግሌዎች የጋራ ማህበር ሊመሰረት ነው

69
ሶዶ ሀምሌ15/2010 በወላይታ ዞን ከመንግሥት ጋር በመሆን የአካባቢውን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የሚያግዝ የሀገር ሽማግሌዎች የጋራ ማህበር ሊመሰረት ነው፡፡ ማህበሩን መመስረት ያስፈለገው በተናጠል ይንቀሳቀሱ የነበሩ ሁለት የወላይታ ዞን የሀገር ሽማግሌዎች ማህበራት አንድ ጠንካራ አደረጃጀት ለመፍጠር እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ የወላይታ ዞን አስተዳደር ማህበራቱን የማደራጀት አቅም የመፍጠርና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ዛሬ በሶዶ ከተማ በተወያየበት ወቅት ሁለቱ አንድ ጠንካራ ማህበር በመሆን  ከመንግሥት ጋር የአከባቢውን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በጋራ ለመስራት እንደተስማሙ ተገልጿል፡፡ በልማትና በመልካም አስተዳደር እንዲሁም ከአጎራባች ዞኖች ጋር አለመግባባቶችን  በማስተካከል ችግሮችን ለመፍታት በጋራ እንደሚሰሩም የሀገር ሽማግሌዎቹ አስታውቀዋል፡፡ ከሃገር ሽማግሌዎች ማህበር አባላት መካከል አቶ ተክሌ ታኪሶ በሰጡት አስተያየት "በዞኑ በተለያዩ ምክንያቶች በተፈጠሩ ክፍተቶች ተቀራርበን መስራት ባለመቻላችን ልማቱም ሆነ የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ለማጠናከር አቅም እንዳያገኙ አድርጓል" ብለዋል የሀገር ሽማግሌዎች ያላቸውን ተሰሚነት በመጠቀም ችግሮችን የመፍታት አቅም ቢኖራቸውም ተቀራርቦ እንዲሰሩና ኃላፊነት እንዲሰማቸው የሚያደርግ አሰራር ባለመኖሩ ጉዳዮች እየተጓተቱ መራራቅ መምጣቱ ሲያሳዝናቸው እንደቆየ አመልክተዋል፡፡ አሁን ላይ የዞኑ አስተዳደር ሁኔታውን በመረዳት ሁለት መልክ ሆኖ አስቸጋሪ የሆነውን አሰራር በማፍረስ የጋራ አደረጃጀት ለመፍጠር በወሰደው ቁርጠኝነት ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ አቶ ተክሌ እንዳሉት ጠንካራ አደረጃጀቱ የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከመስራት ባሻገር ከአጎራባች ዞኖች ጋር የሚከሰቱ ችግሮችን በሰከነ መልኩ ለመፍታት የሚያስችል ዕድል ይፈጥራል፡፡ ከባህል ታርክና ቅርስ ተንከባካቢ ማህበር አቶ ወልደማሪያም ልሳኑ በበኩላቸው በመከፋፈል የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት በሚያስቡ ግለሰቦች አማካኝነት የሀገር ሽማግሌ ማህበር ለሁለት እንዲሆኑ በመደረጉ ለችግር ማጋለጡን ተናግረዋል፡፡ የሀገር ሽማግሌዎች ከአመራሩ ጋር ባለመቀራረባቸው የማህበረሰቡ ነባርና ባህላዊ እሴቶች አደጋ ላይ እንዲወድቁ መድረጉን አመልክተው  ለበርካታ ቅሬታዎች ዋንኛ መንስኤ ሆኖ መቆየቱንም ጠቅሰዋል፡፡ በጋራ ለመሆን የተጀመረውን አካሄድ በመደገፍ በቅንጅት መንቀሳቀስ ወሳኝ መሆኑን የተናገሩት አቶ  ወልደማሪያም በየአካባቢው የሚነሱ የጸጥታ ችግሮችን አባቶች ቀድሞም በባህላዊ መንገድ  በዘላቂነት መቆጣጠር እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡ መንግስት ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረት አበረታች በመሆኑ ልምዶችን በማካፈል የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል፡፡ የወላይታ ሽማግሌዎች በሁለት ማህበር በመከፋፈል ስልጣናቸውን ለማራዘም በተዘረጋው ወጥመድ የህዝብን ሃብትና ንብረት በሙሰኞች እጅ እንዲወድቅ ማድረጉን የተናገሩት ደግሞ አቶ ዳንኤል ደሳለኝ  ናቸው፡፡ ይህ በመንግስት ላይ ያላቸው ዕምነት እንዲሸረሽር ማድረጉን ጠቁመው መንግስት በአሁኑ ሰዓት ተጠያቂነትን ለማስፈንና ብሄራዊ አንድነትን ለማምጣት መጀመሩ እንዳነቃቃቸውና በጋራ ለመስራትም  መዘጋጀታቸውንም  ተናግረዋል፡፡ የወላይታ ዞን ተጠባባቂ ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ጌታሁን ጋረደው እንዳመለከቱት በዞኑ ሁለት የተለያዩ የሀገር ሽማግሌዎች ማህበር መኖሩ መልካም ዕድል ቢሆንም አመራር ከመስጠትና ተቀናጅቶ ከመሥራት አንጻር ጉድለቶች ታይተዋል፡፡ የሽማግሌዎች አደረጃጀት ሲጠናከር በአካባቢው በተለይም ለመልካም አስተዳደርና ለብልሹ አሰራር የሚያጋልጡ አሰራሮችን በማጋለጥና ግልጽነት ያለው አሰራር  በማጠናከር  የህበረተሰቡን የሰላምና የልማት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡ በዚህም የሀገር ሽማግሌዎች በመደመርና አብሮ በመሥራት ከአከባቢውም ልማት ባሻገር ከአጎራባች ዞኖች ጋር የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በጋራ ለማስማማት  የሚያስችል ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ዶክተር ጌታሁን ገልጸዋል፡፡ የህዝቡንና የአከባቢውን ሰላምና ጸጥታ ለማናጋት የሚሰሩ ኃይሎችን በመቆጣጠር ረገድ የሀገር ሽማግሌዎች የሚጠበቅባቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመው አስተዳደሩም ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡ በውይይቱ ከዞኑ12 የገጠር ወረዳዎችና ሶስት የከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ከ130 በላይ የሃገር ሽማግሌዎች የተሳተፉ ሲሆን በቀጣይ የጋራ ማህበራቸውን ለመመስረት ተስማምተዋል፡፡ በተናጠል ይንቀሳቀሱ ነበሩት ሁለቱ ማህበራት የወላይታ ባህል ታርክና ቅርስ ተንከባካቢ ማህበር  እና የሃገር ሽማግሌዎች ማህበር በሚል ከመንግስት ዕውቅና ያገኙ መሆናቸውን የዞኑ ባህል ቱሪዝምና የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም