በብራይት ስታር ኤንድ ኤቨሎፕመንት አሶሴሽን ለሚደገፉ ወገኖች የከተማ አስተዳደሩ የምሳ ግብዣ አደረገ

1710

አዲስ አበባ ታህሳስ 29/2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገና በዓልን በማስመልከት በብራይት ስታር ኤንድ ኤቨሎፕመንት አሶሴሽን ለሚገኙ ታዳጊዎችና ወጣቶች የምሳ ግብዣ አደረገ።

የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ አለሙ ከተማ አስተዳሩን በመወከል የምሳ ግብዣውን አድርገዋል።

ከታዳጊዎችና ወጣቶች ጋር በዓሉን በማሳለፋቸው መደስታቸውን ገልጸው ከሚበላው ምግብ ባለፈ የአብሮነት የመረዳዳትና የመተዘጋገዝ መንፈስ ጎልቶ የሚታይበት ነው ብለዋል።

ብራይት ስታር ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን በችግር ውስጥ የነበሩ ዜጎችን ሕይወት ለመቀየር እያከናወነ ያለው ተግባር መበረታታት የሚገባው በጎ ስራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በአሶሴሽኑ ስር ሕይወታቸው የተቀየሩ ታዳጊዎችና ወጣቶች አገርን በሚያለሙና በሚጠቅሙ ስራዎች ለመሳተፍ ራዕይ ሰንቀው ከወዲሁ መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

በአሶሴሽኑ የሚገኘውን የታዳጊዎች ማቆያም በዚሁ አጋጣሚ የጎበኙት አቶ መለሰ፤ ብራይት ስታር ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን ለሚያከናውናቸው ስራዎች አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የብራይት ስታር ሪሊፍ ኤንድ ዴቬሎፕመንት አሶሴሽን የፕሮጀክቶች አስተባባሪ አቶ በፍርዱ መሰረት በበኩላቸው አሶሴሽኑ ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ሕይወት ማሻሻል ላይ በተለይም ኑሯቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ ወጣቶችና ሴተኛ አዳሪዎች ሕይወትን መቀየር ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

አሶሴሽኑ ባስገነባቸው ሶስት ትምህርት ቤቶች ከ1 ሺህ በላይ ታዳጊዎች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በአማራጭ ትምህርት መርሃ ግብር የትምህርት እድል ያላገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ድጋፍ በማደረግ እንደሚሩ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሶሴሽኑ ስር ድጋፍ የሚደረግላቸው ወጣቶችና ታዳጊዎች በተዘጋጁ የማቆያ ማዕከላት እንዲሁም ክሊኒክ የሚያስፈልጋቸውን አገልግሎት እንዲያገኙ እንደሚደረግም ገልጸዋል።

ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን ባለፈው ዓመት 200 ኑራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎችን በማንሳት ከነዚህ ውስጥ ደግሞ 160 ዎቹ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ መደረጉን ነው አቶ በፍርዱ ያስረዱት።

በቀጣይ  አንድም ልጅ ጎዳና ላይ መኖር የለበትም በሚል መርሃ ማቆያ ማዕከላትን የማስፋፋትና አሶሴሽኑ የሚያስተምራቸውን ሰዎች ቁጥር ለመጨመር እቅድ ይዟል ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ አሶሴሽኑ ለሚያከናውናቸው ተግባራት የመስሪያ ቦታ ድጋፍ እንዲያደርግም አቶ በፍርዱ ጥሪ አቅርበዋል።

በአሶሴሽኑ ድጋፍ የሚደረግላቸው ታዳጊዎችም ከጎዳና ኑሮ ተላቀው ለነገ ሕይወታቸው ተስፋ እንደሰነቁ በመግለጽ በትምህርታቸው የተሻለ ደረጃ ለመድረስ እንደሚጥሩም ተናግረዋል።

የገና በዓልን አስመለክቶ ለተደረገላቸው የምሳ ግብዣም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ብራይት ስታር ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን በ2007 ዓ.ም የተቋቋመ መንግስታዊ ያልሆነ የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው።