የጀግኖች አምባ እና ህፃናት አምባ በተጠናከረ መልኩ እንዲቋቋሙ ይደረጋል - ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ

111

ታህሳስ 29/2013 (ኢዜአ) የጀግኖች አምባ እና ህፃናት አምባ በተጠናከረ መልኩ እንዲቋቋሙ የሚደረግ መሆኑን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ አስታወቁ፡፡

የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና የአገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች ከጦር አካል ጉዳተኞች ጋር የገና በአልን አክብረዋል።

የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ "የጦር ጉዳተኞቹ ለአገርና ለህዝብ ሲሉ ህይወታቸውንና አካላቸውን የሰጡ በመሆናቸው ልናከብራቸው ይገባል" ብለዋል።

የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ዘላቂ እንክብካቤ ያገኙበትና በስሙ ይኮሩበት የነበረው ጀግኖች አምባ “ከኛ በፊት ጀግንነትም ጀግናም የለም” ይሉ በነበሩ ጽንፈኞች መዘጋቱን አስታውሰው፤ በቀጣይ የጀግኖች አምባ እና ህፃናት አምባ በተጠናከረ መንገድ እንደገና እንዲቋቋሙ የሚደረግ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የትናንቱን የጀግንነት ተግባር መካድ የዛሬን ጀግንነት መካድና ለነገም የማይጠቅም ፍፁም የተሳሳተ ድርጊት መሆኑንም ጠቅሰው፤ እነዚህ ተቋማት ከወደቁበት ተነስተው አገልግሎት እንዲሰጡ መወሰኑን ገልጸዋል።

መንግሥት የአካል ጉዳተኞችን መብት፣ ክብር፣ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል፡፡

ሚኒስቴሩ የአካል ጉዳተኞችን እንዲሁም የጦር አካል ጉዳተኛ ጀግኖችን ለማገልገል ከመቼውም ጊዜ በላይ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው "ጀግንነት የትውልድ ቅብብሎሽ በመሆኑ በዚሁ ሂደት ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ተከብረው ዘልቀዋል" ብለዋል።

ለዚህ ክብር የጦር ጉዳተኞቹ ታላላቅ ጀብድ የሰሩና ለአገርና ለህዝብ ህይወታቸውንና አካላቸውን መስዋዕት ያደረጉ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

"በመሆኑም ከጦር ጉዳተኞች ጋር በዓል ማክበር ብቻ ሳይሆን ማዕከሉ ለትውልድ እንዲያገለግል ብዙዎች የሚማሩበትና የዜጎች ኩራት ሆኖ እንዲቀጥል ይደረጋል" ብለዋል።

በየመስኩ የትውልድ ጀግንነት እንደሚቀጥል አውስተው፤ "ጀግንነት ሊከበር፣ ሊወደስና ቦታ ሊሰጠው ይገባል" ብለዋል።

ምክትል ከንቲባዋ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተለገሱትን 30 በጎችም በእለቱ አስረክበዋል።

በደቡብ ሱዳን ቆንስላ ጽህፈት ቤት የሚገኙ አንድ ኢትዮጵያዊም ለማህበሩ 300 ሺህ ብር መለገሳቸውን በፕሮግራሙ ላይ ተጠቅሷል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ እንዲሁም ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም