ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤ በቃሊቲ ጊዚያዊ ማቆያ ከሚገኙ ከጎዳና ከተነሱ ዜጎች ጋር ገናን አከበሩ

114

ታህሳስ 29 / 2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ጋር በመሆን በቃሊቲ ጊዚያዊ ማቆያ ከሚገኙ ከጎዳና ከተነሱ ዜጎች የገና በዓልን አክብረዋል።

በመርሐግብሩ ምክትል ከንቲባዋ እንደገለፁት፤ በተያዘዉ በጀት ዓመት 8 ሺህ 286 በጎዳና ላይ ይኖሩ የነበሩ ወጣቶችን በማንሳት የሙያ ክህሎት እና የስነ-ልቦና ስልጠናዎች ተሰጥተዋል።

በዚህም እስካሁን በሰባት ክፍለ ከተሞች እና በአቃቂ ጊዜያዊ ማቆሚያ ማዕከል 3 ሺህ 966 የሚሆኑት ወጣቶች ተገቢዉን የሙያ እና የስነ-ልቦና ስልጠና አጠናቀው በደረቅ ቆሻሻ፣ አረንጓዴ ልማትና መንገድ ጥርጊያ ላይ የስራ እድል ለመፍጠር ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።

"ጎዳና ጊዜያዊ የህይወት መምሪያችሁ ሆኖ ቆይቷል" ያሉት ምክትል ከንቲባዋ፤ "አሁን ያ ጊዜ አልፎ በሌላ የህይወት ምዕራፍ ላይ ተገኝታችኋል" ብለዋል።

አያይዘውም ፈተና ለእናንተ አዲስ አይደለም፤ "በጎዳናም ብዙ ፈተና አልፋችሁ ስለመጣችሁ የወሰዳችሁትን ስልጠና ወደ ተግባር ቀይራችሁ ለሚገጥማቸዉ ፈተና እጅ ሳትሰጡ ራሳችሁንና አገራችሁን እንድትለውጡ" ሲሉ የአደራ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በማዕከሉ የተህድሶ ስልጠና በመውሰድ ላይ የሚገኙ ወጣቶች በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ ከጎዳና ህይወት እንዲወጡ ለማስቻል ለሰጣቸው የህይወት ክህሎት ስልጠና እና ለተፈጠረላቸው የስራ እድል ማመስገናቸውን የአስተዳደሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት አመልክቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሩ በአቃቂ ክፍለ ከተማ ለሚገኘው የአረጋውያን መርጃ ማዕከል ለገና በዓል ማክበሪያ የሚሆን የዕርድ ሰንጋ በስጦታ አበርክቷል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም