በደሴ ከተማ በዓሉን በማስመልከት ለተችግር ለተጋለጡ ወገኖች 200 ኩንታል የስንዴ ዱቄት ድጋፍ ተደረገ

65

ደሴ ታህሳስ 29/2013( ኢዜአ ) የደሴ ከተማ አስተዳደር የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ ለችግር ለተጋለጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች 200 ኩንታል የስንዴ ዱቄት ድጋፍ አደረገ።

የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አበበ ገብረ መስቀል ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት ገና ያለው ለሌለው በማካፈል ተረዳድቶ የሚዋልበት  በዓል ነው።

ለዚህም ከተማ አስተዳደሩ  ለችግር ለተጋለጡ  አካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን ጨምሮ  ለ740  የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ መደረጉን አስረድተዋል።

ድጋፉ ግማሽ ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የስንዴ ዱቄት በነፍስ ወከፍ  25 ኪሎ ግራም  እንዲደርሳቸው መደረጉን ገልጸዋል።

ከንቲባው ሁሉም ያለውን እያካፈለ በዓሉን በአንድነት፣ ደስታና አብሮነት ማሳለፍ እንዳለበት  አመልክተው ፤የወሎን የመረዳዳትና የፍቅር ተምሳሌ በተግባር የማሳየት ኃላፊነታችን መወጣት ይጠበቅብናልም ብለዋል፡፡

የከተማዋ አስተዳደር አቅሙ በፈቀደ የተቸገሩ ወገኖችን  በማገዝ የጀመረውን ጥረትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል ወይዘሮ ወርቅዬ በላይ በሰጡት አስተያየተ የተደረገላቸው ድጋፍ በዓሉን በደስታ እንዲውሉ የሚያግዛቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ደስተኛ እንደሆኑ ጠቁመው፤ሁሉም ያለውን በማካፈል ኢትዮጵያ የአብሮነትና የመልካምነት እሴት ማስቀጠል ይኖርበታልም ብለዋል፡፡

አቶ አወል ይማም በበኩላቸው የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ ከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ ያደረገላቸው 25 ኪሎ ግራም ዱቄት ጊዜያዊ ችግራቸውን እንደፈታላቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም