የገና በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ የአገር ሃብት እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ

181

አዲስ አበባ ታህሳስ 29/2013 (ኢዜአ) የገና በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ የአገር የቱሪዝም ሃብት እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።

በሚኒስቴሩ የባህል እሴቶች ልማት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ማስረሻ አበበ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት የገና በዓል አከባበር ውብ የሆነውን ኢትዮጵያዊ መልኩን ይዞ እንዲቀጥል ማድረግ ያስፈልጋል።

የገና በዓል በተለያዩ አገራት የሚከበር ቢሆንም በኢትዮጵያ ግን አከባበሩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቹ ተዳምረው ልዩ እንደሚያደርጉት ገልጸዋል።

በመሆኑም በዓሉ ኢትዮጵያዊ መልኩን እንደያዘ የሀገር የቱሪዝም ሃብት ሆኖ እንዲቀጥል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የገና በዓል የገና ጨዋታን ጨምሮ በርካታ ጥልቅ ይዘት ያላቸው እሴቶች አንዳሉት የገለጹት አቶ ማስረሻ የሚጎበኝና የቱሪስቶች አይን ማረፊያ እንዲሆን መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

አሁን ላይ የእኛ መገለጫዎች ያልሆኑና የማይጠቅሙ ጎጂ መጤ ባህሎች ስላሉ እሴቶቻችን እንዳይበረዙ መጠበቅና መጠንቀቅ ያስፈልጋልንም ነው ያሉት።

በመሆኑም የገና በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን አንደተላበሰ ለትውልድ ማስተላለፍ የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያኖች ልዩ የሚያደርጉንን የበዓል አከባበር ይዘቶች የምንጠብቀው በጋራ ነው ያሉት አቶ ማስረሻ ይዘቶቹ እንዳይጠፉና እንዳይበረዙ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከማይጠቅሙና ጎጂ መጤ ባህሎች ትውልዱ እየተጠነቀቀ ኢትዮጵያዊ ማንነቱን ማጉላትን፣ ባህሉን ማበልፀግና ማሳደግ እንዲሁም የአገር የቱሪዝም ሃብት እንዲሆን መስራት የኖርበታልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም