የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰራተኞች የመብትና የኢኮኖሚ ጥያቄያቸው እንዲከበር ጠየቁ

278
አዲስ አበባ ሐምሌ 15/2010 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰራተኞች የመብትና የኢኮኖሚ ጥያቄዎቻቸው እንዲከበሩ ጠየቁ። የባንኩ ሰራተኞች መሰረታዊ ማህበር አመራር ዛሬ ከጠቅላላ ሰራተኞቹ ጋር ውይይት አድርጓል። የመዋቅር ምደባ፣ ደመዋዝና ሌሎች የሰራተኞች መብትና ጥቅማጥቅም ጥያቄዎች የውይይቱ አጀንዳዎቸ ነበሩ። በውይይቱ የተሳተፉት የባንኩ ሰራተኞች የህብረት ስምምነት ጥሰት ይቁም፣ በመዋቅሩ ይመለሳል የተባለው የደመዋዝ ጥያቄ ይስተካከል፣ እንደዚሁም የሰራተኞች ቅሬታዎቸ ይፈቱ የሚሉ ጥያቄዎችን አቅርበዋል። ባንኩ ከአንድ ወር በፊት ተግባራዊ ያደረገው መዋቅር ሰራተኛው ያልተወያየበት መሆኑን የገለፁት ተሰብሳቢዎቹ፤ የተቀመጡት የስራ ደረጃዎች ግልጽ ካለመሆናቸውም በተጨማሪ ምደባው ፍትሃዊነት ይጎድለዋል የሚሉ ቅሬታዎችንም አንስተዋል። አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰጡ የባንኩ ሰራተኞች የደመዋዝና ጥቅማጥቅም እንዲሁም ሌሎች የመብት ጥያቄዎችን ለረዥም ጊዜ ቢያቀርቡም መልስ እንዳልተሰጣቸው ነው የተናገሩት። አቶ ያስቤድ ተስፋዬ የተባሉ የባንኩ ሰራተኛ "በመዋቅሩ የተሰራው ምደባ ፍትሃዊ አይደለም፣ መስፈርቶቹ በግልጽ ተቀምጠው ሳይሆን መሾም የሚፈለገው ሰው እንዲያድግ በአለቆች መልካም ፈቃድ የተሰራ ነው" የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። በባንኩ አምስት ዓመት ማገልገላቸውን የሚናገሩት አቶ ያስቤድ ከእሳቸው በታች የስራ ልምድ ያላቸው እድገት አግኝተው እርሳቸውን ግን አድገት እንዳልተሰጣቸው ገልፀዋል። ይህም በባንኩ ወጥነት የጎደለው አሰራር መኖሩን ያሳያል ብለዋል። አቶ ቢኒያም ዋቄ ሌላ ሰራተኛ በበኩላቸው "ለአገልግሎታችን ተገቢ ክፍያ ይክፈለን፣ አድሏዊ አሰራር ይቅር፣ እድገት ለማግኘት የሰራተኛው ብቃት እንጂ ዝምድና አይታይ" የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። ከእርሳቸው በታች ያሉ ሰራተኞች እስከ ሶስት ደረጃ እድገት ሲያገኙ፤ በእሳቸው ደረጃ ያሉ ደግሞ ወደ አስተዳደር ሲያድጉ እርሳቸው ግን እድገት አለማግኘታቸውን ነው የተናገሩት። በባንኩ ውስጥ አዳዲስ አሰራሮች ተግባራዊ የሚሆኑት ሰራተኛው ሳይወያይባቸው ነው የሚሉት ደግሞ አቶ ዘሪሁን በቀለ የተባሉ ሰራተኛ ናቸው። "የትርፍ ሰዓት ክፍያ እየተከፈለ አይደለም" ያሉት እኚህ አስተያየት ሰጪ "የቆየ የደመዋዝ ጥያቄ በመዋቅር ይመለሳል ብለን ብንጠብቅም አልተመለሰም ስለዚህ የመብትና የኢኮኖሚ ጥያቄያችን ሊታይልን ይገባል" ብለዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰራተኞች መሰረታዊ ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ሃይማኖት ለማ የህብረት ስምምነት ጥሰት መቆም አንዳለበት ጠቅሰው  "በመዋቅሩ የተሰራው የደመዋዝ ስኬል አፈጻጸም መጥቶ ቅሬታዎች እስኪፈቱ በስራችን አንቀጥላለን" በማለት ተናግረዋል። መዋቅሩ ሲሰራ እንደ ሰራተኛ ተወካይ ውይይት እንዳላደረጉ የሚገልፁት የማህበሩ ፕሬዝዳንት አሁን ይፋ በሆነው መዋቅር ላይ የተቀመጡት መስፈርቶች "ለአድሏዊ አሰራር የተመቹ ሆነው የተዘጋጁ ናቸው" ብለዋል። በመዋቅሩ ትግበራ ላይ በሰራተኛው ዘንድ በርካታ ቅሬታዎች እየተነሱ መሆኑን በመግለጽ የተነሱ ጥያቄዎች እንዲፈቱ ማህበሩ ለበላይ ሃላፊዎች ጥያቄ ማቅረቡን ነው የገለጹት። እንደ አቶ ሃይማኖት ገለጻ በቅርቡ በጥያቄዎቹ ዙሪያ ከባንኩ ፕሬዝዳንት ጋር ውይይት በማድረግ የመዋቅሩ ተግባራዊነት እንዲቆም ስምምነት ላይ ተደርሷል። የአሰሪና ሰራተኛ የህብረት ስምምነት ጥሰትን ጨምሮ ሌሎች የተነሱ የሰራተኛው ጥያቄዎች ካልተመለሱ ወደ ስራ ማቆም አድማና ሰላማዊ ሰልፍ እርምጃዎች አንደሚገቡም አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰራተኞች መሰረታዊ ማህበር በ1960ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን ከ20 ሺህ በላይ አባላት አሉት። በዛሬው መድረክም ከ2 ሺህ በላይ አባላት ተገኝተው በመብትና ጥቅሞቻቸው ላይ ውይይት አድርገዋል። በውይይቱ ላይ የባንኩ ፕሬዝዳንትም ይሁን ተወካይ አልተገኙም፣ መድረኩ ሰራተኞች ችግሮቻቸውን የሚወያዩበት መሆኑንም ከማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ሃይማኖት ለማ ሰምተናል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም