ባለፈው ዓመት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተተከሉት ችግኞች 80 በመቶ መጽደቁን ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ

62

አዲስ አባበ፤ ታህሳስ 28/2013(ኢዜአ) ባለፈው ዓመት ክረምት በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተተከሉት 5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ችግኞች መካከል 80 በመቶው መፅደቁን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በቀጣዩ ክረምት በመላ አገሪቷ 6 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ ባለፉት ስድስት ወራት በተቋሙ የተከናወኑና በቀጣይ ስለሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በቀጣዩ ክረምት በመላ አገሪቷ 6 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም 39 ሺህ 973 ችግኝ ጣቢያዎችን የማደስና ለችግኝ ማፍያነት ዝግጁ የማድረግ ስራ ተጀምሯል ብለዋል።ከዚህ በተጨማሪ 1 ቢሊዮን ችግኞችን በማዘጋጀት ለጎረቤት ሃገራት ለማከፋፈል መታቀዱን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰዋል።

ባለፈው ዓመት ክረምት በመላ አገሪቷ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትክል ታቅዶ 5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል መቻሉንም ገልጸው፤ ከተተከሉት ችግኞች መካከል 80 በመቶው መጽደቁን አስታውቀዋል።

ለችግኞች መጽደቅ የህብረተሰቡ፣ የማህበራትና የተቋማት ርብርብ ከፍተኛ እንደነበርም ተናግረዋል።

ከተተከሉ ችግኞች መካከል በርካቶቹ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያግዙ ጥምር ደንና የፍራፍሬ ችግኞች እንደነበሩም አስታውሰዋል።

የዘንድሮውን የውሃና የአፈር ጥበቃ ስራን በተመለከተም የዝግጅት መዕራፉ ተጠናቆ ወደ ትግበራ ምዕራፍ በመገባት ላይ መሆኑን አብራርተዋል።

በእቅዱ መሰረት 835 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እንደሚሰራ ገልጸው፤ በመርሃ ግብሩ ከ7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች እንደሚሳተፉም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም