ሰብልን በኮምባይነር በመሰብሰባችን የምርት ብክነት አስቀርተናል... አርሶ አደሮች

99

ጎባ፤ታህሳስ 28/2013 (ኢዜአ) በመኽር ወቅት ያለማነውን ሰብል በኮምባይነር በመሰብሰባችን የምርት ብክነትን አስቀርተናል ሲሉ በባሌ ዞን የሲናና ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።

በዞኑ ኮምባይነርና የሰው ጉልበት በመጠቀም በ124 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ የነበረ የደረሰ ሰብል ተሰብስቧል።

የሲናና ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አዱኛ ከተማ ለኢዜአ እንደገለጹት በመኸር ወቅት በሶስት ሄክታር ማሳቸው ላይ ያለሙትን ስንዴ በኮምባይነር አጭደውና ወቅተው ሰብስበዋል።

ባለፈው አመት አጭደው ለመውቃት በኩንታል 150 ብር ይከፍሉ የነበረው የኮምባይር ኪራይ በዚህ አመት ወደ 50 ብር ዝቅ እንዳለላቸውም ተናግረዋል ።

ሰብልን በኮምባይነር አጭደው በመውቃታቸው ከዚህ ቀደም ለሰው ጉልበት የሚፈጅባቸውን ጊዜና  ወጭ ከመቀነሳቸው ባለፈ የምርት ብክነትን ማስቀረታቸውን ነው የገለጹት።

"በተለይም ዘንድሮ ሰብላችንን ፈጥነን በኮምባይነር በመሰብሰባችን ምርታችንን ከአንበጣ መንጋና ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ልንታደግ ችለናል" ብለዋል።

በሰው ጉልበት የሚሰበሰበው ሰብል ታጭዶ፣ ሲከመርና ሲወቃ ባለው ሂደት በአእዋፍ፣ በተባይ፣ በአይጥ፣ በዝናብና በሌሎች ምክንያቶች የምርት ብክነት ያጋጥም እንደነበር ያስታወሱት ደግሞ አርሶ አደር ሀሰን አልይ ናቸው፡፡ 

ዘንድሮ ኮምባይነር በመጠቀም በሰዓታት ውስጥ ሰብላቸውን ሰብስበው በመውቃታቸው የምርት ብክነትም ሆነ የጥራት መጓደል እንዳላጋጠማቸው አመልክተዋል።

በዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ኃብት ልማት ጽህፈት ቤት የሰብል ልማት ባለሙያ ወይዘሮ አልማዝ ኃይሉ በዞኑ በመኽር ምርት ወቅት ከ258 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የሰብል መልማቱን ተናገረዋል፡፡

በምርት ወቅት በተለያዩ  ሰብሎች ከለማው ማሳ ውስጥ በ124 ሺህ ሄክታር ላይ የነበረ የደረሰ ሰብል በኮምባይነርና  በሰው ጉልበት በመታገዝ መሰብሰቡን አመልክተዋል፡፡

ባለሙያዋ እንዳሉት በዞኑ አምስት ወረዳዎች ውስጥ እስከ አሁን ከተሰበሰበው ሰብል 62 ሺህ ሄክታሩ 130 በሚሆኑ የአጭዶ መውቂያ ኮምባይነሮች በመታገዝ የተሰበሰበ ነው፡፡ 

በዞኑ በ2012/13 ምርት ዘመን መኽር ወቅት ከለማው ሰብል 7 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም