ሕዝበ ክርስቲያኑ የገናን በዓል ሲያከብር ከመተጋገዝና ከመደጋገፍ ባሻገር ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላም በአንድነት ሊሰራ ይገባል...የሐይማኖት አባቶች

77

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 28/2013(ኢዜአ) ሕዝበ ክርስቲያኑ የገናን በዓል ሲያከብር ከመተጋገዝና ከመደጋገፍ ባሻገር ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላም በአንድነት ሊሰራ እደሚገባ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አሳሰበች።

ምእመናን የገናን በአል ሲያከብሩ የተቸገሩና ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በመርዳት መሆን እንዳለበትም የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መልእክቷን አስተላልፋለች።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹ አቡነ ማቲያስ፤ በነገው እለት የሚከበረውን የእየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

በዓሉ የታመሙትንና በማረሚያ ቤት ያሉትን በመጠየቅ፤ የተራቡን በመመገብ፣ የተጠሙትን በማጠጣትና የታረዙትን በማልበስ ለፈጣሪና ለወገናችን ያለንን ክብር የምናሳይበት ነው ብለዋል።

''የክርስቶስ ልደት ሰማያዊያንና ምድራውያን ስለ ክርስቶስ ክብርና ሰላም በሕብረት የዘመሩበት'' በመሆኑ ሕዝበ ክርስቲያኑም በበጎ ስራ በጋራ በመሳተፍ በዓሉን ማክበር እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

በአሁኑ ወቅት ''በሀገሪቱ በገጠርና በከተማ በየአቅጣጫው እየተከሰተ ያለው ችግር ልማታችንን ፣ ነፃነታችንና ሉዓላዊነታችን የሚፈታተን ስለሚሆን ጥንቃቄ መውሰድ ይገባል '' ሲሉ ጠቁመዋል።

ለዚህም መላው ሕዝብ በጥበብና በማስተዋል እንዲንቀሳቀስ፣ ሁሉም ለሀገሩ፣ ለሃይማኖቱ፣ ለወገኑም ተገቢ ትኩረት በመስጠት በፀሎትና በሚችለው ሁሉ ትብብሩን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ የሱስ በበኩላቸው "ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአሉን ሲያከብርም  ሆነ ከዚያም በኋላ ያለ ልዩነት እርስ በርስ በመተጋጋዝና በመደጋጋፍ ለሀገር ሰላምና አንድነት በጋራ በመቆም ሊሆን ይገባል'' ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት መንግስት በመላው ሀገሪቱ  ሰላም ለማስፈንና የህግ የበላይነት ለማስከበር የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

የአገር ደህንነትንና የዜጎችን ሰላም በማስጠበቅ ኃላፊነት ተሰማርተው ለሚገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አባላትም መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

ህብረተሰቡ ወቅታዊ የጤና ስጋት ከሆነው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ራሱን እንዲጠብቅም ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም